ቀጥታ፡

የጥፋት ቡድኑን በመታገል ለትግራይ ሰላምና ልማት የበኩላችንን እንወጣለን - የትግራይ ተወላጆች

ሐረር/አሶሳ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ ለጥፋት የቆመውን የህወሓት ቡድን በመታገል ለትግራይ ሰላምና ልማት የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ በሐረር እና በአሶሳ ከተሞች የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ።

የትግራይ ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የህወሃትን የጥፋት ቡድን በጽኑ ሊታገል ይገባል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰሞኑን በትግርኛ ቋንቋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የትግራይ ህዝብ ለሰላም እና ልማት የታገለ እንደሆነ ጠቁመው የሰላም እና ልማት ፍላጎቱ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል። 

በሁሉም ክልሎች እየመጣ ያለው ልማትና ሰላም የትግራይ ህዝብም ይገባዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረጀ አስተሳሰብ ለዳግም ጦርነትና ውድመት የሚጥረው የሕወሓት ቡድን ተው ሊባል ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በሐረር እና በአሶሳ ከተሞች ኢዜአ ያነጋገራቸው የትግራይ ተወላጆች፤ የህወሓት ቡድን ከጥፋትና የጦርነት እቅድ በስተቀር ለህዝብ ሰላምና ልማት መስራት የማይፈልግ ስብስብ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቡድኑን እኩይ ዓላማ እና የህዝቡን የሰላምና የልማት ፍላጎት በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ተክክለኛ እና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ በመደገፍ ለጥፋት የቆመውን ቡድን በመታገል ለትግራይ ሰላምና ልማት የበኩላችንን እንወጣለን ነው ያሉት።


 

በሐረር ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ጊዮርጊስ ሃጎስ፤ የጥፋት ቡድኑ መቼም ቢሆን ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት ሰርቶ የማያውቅ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት ከማይሻው የሻዕቢያ መንግስት ጋር ግንባር በመፍጠር አካባቢውን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ይህንን እኩይ ዓላማ በፅኑ እንታገለዋለን ብለዋል።


 

የአሶሳ ከተማ ነዋሪው ጎይቶም በየነ፤ የህወሓት የጥፋት ቡድን እሳቤ ጊዜው ያለፈበትና ለማንም የማይጠቅም መሆኑንና የትግራይ ህዝብ አሁን ላይ እንደሌሎች ክልሎች በአዲስ እሳቤና በአዲስ ትውልድ መመራትን አጥብቆ ይሻል ብለዋል።

በመሆኑም የህወሓትን ቡድን ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ በጋራ በመታገል ለክልሉ ሰላም፣ ልማትና ተጠቃሚነት በተባበረ አቅም እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

በሐረር ከተማ የሚኖረው ሼኖክ ሊላይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያስተላለፉት መልእክት ለሀገር ሰላምና ልማት የሚጠቅም በመሆኑ ሁላችንም የምንደግፈው ነው ብሏል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሌሎች ክልሎች ሁሉ ለትግራይ ክልል ህዝብ ሰላም፣ ልማትና እድገት ያስፈልገዋል ማለታቸው ተገቢ መሆኑን አንስቶ ለዚህም በተለይም የክልሉ ተወላጆች የበኩላችንን እንወጣለን ሲል ተናግሯል። 

ሌላኛው በአሶሳ ከተማ የሚኖረው ወጣት ክብሮም ገብረመድህን፤ በኢትዮጵያ ከመጣው ለውጥና ሁለንተናዊ የልማት እቅዶች ተጠቃሚ ለመሆን የትግራይ ህዝብ አጥብቆ ይሻል ሲል ገልጿል።


 

ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ለግጭትና ጦርነት እየሰራ የሚገኘውን የህወሓት የጥፋት ስብስብን በጋራ መታገል ሲቻል ብቻ መሆኑን ገልፆ ለዚህም በተለይ ወጣቶች አደራችንን ለመወጣት እንሰራለን ብሏል።


 

በሐረር ከተማ ያገኘናቸው ወጣት ሳሙኤል መለስ እና ወጣት ፍሬህይወት ብርሃነ፤ የትግራይ ወጣቶች አሁን ላይ የህወሓትን የጦርነት ነጋሪት ሸሽተው እየተሰደዱ መሆኑን አንስተው ነገር ግን ስደት መፍትሄ የማያመጣ በመሆኑ ለትግራይ ህዝብ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ለውጥ እንዲመጣ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም