ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የህወሃትን የጥፋት ቡድን በጽኑ ሊታገል ይገባል

አሶሳ/አዳማ/ሶዶ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የህወሃትን የጥፋት ቡድን በጽኑ ሊታገል ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ከኢዜአ ጋር በትግርኛ ቋንቋ በነበራቸው ቆይታ የትግራይ ህዝብ ለሰላም እና ልማት የታገለ መሆኑን አንስተው የሰላም እና ልማት ፍላጎቱ ትልቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሰሜኑ ጦርነት የተከሰተው ህወሓት ለውጥን ባለመቀበሉ እና ያረጀ እሳቤን የማስቀጠል አባዜ ምክንያት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

በሁሉም ክልሎች እየመጣ ያለው ልማትና ሰላም የትግራይ ህዝብም ይገባዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረጀ አስተሳሰብ ለዳግም ጦርነትና ውድመት የሚጥረው የህወሃት ቡድን ተው ሊባል ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ ለሰላም እና ልማት የታገለ ጠንካራ ህዝብ መሆኑን አንስተው መንግስት የህዝቡን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ለማገዝና ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአሶሳ፣ አርሲ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን የክልሉን ህዝብ የሰላም መሻትና ለጥፋት የሚንቀሳቀሰውን የህወሃት ቡድን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ ወሳኝ መልእክት የተላለፈበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የትግራይ ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የህወሃትን የጥፋት ቡድን በጽኑ ሊታገል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።


 

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ ጅባት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ማብራሪያ የትግራይ ህዝብ ለሰላም እና ልማት የታገለ መሆኑን በማንሳት የህወሃት ቡድን ከዚህ በተቃራኒ ለግጭትና ጦርነት እያደረገ ያለውን ዝግጅት ያስገነዘበ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የክልሉ ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የህወሃትን የጥፋት ቡድን በጽኑ ሊታገል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግስት ያሳየው ሆደ ሰፊነት የትግራይን ህዝብ የሰላም ፍላጎት የተረዳ እንዲሁም የጦርነትን አስከፊነት የተገነዘበ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ታሪክ ተመራማሪና መምህር ሙሐመድ ነሞ (ዶ/ር)፣ የትግራይ ህዝብ ለሰላም የተከፈተው በር እንዳይዘጋ ለጦርነት የሚቀሰቅስን የጥፋት ቡድን አጥብቆ መቃወምና መታገል አለበት ብለዋል።


 

በቆየ አስተሳሰብ ተቸንክሮ የሚገኘው የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ ለብዙ ችግርና እንግልት እየዳረገው መሆኑን ገልጸው ከዚህ በኋላ ገለል ማለት እንዳለበት ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ (ዶ/ር) ማብራሪያ የህውሃት ቡድንን እኩይ ዓላማ ያጋለጠ እና የህዝቡን ሰላም፣ የመልማትና የተጠቃሚነት መብት መሰረት ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጳውሎስ ባልቻ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መንግሥት ለሰላምና ልማት ያለውን ጠንካራ አቋም ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከሰሞኑን ለትግራይ ህዝብ ያስተላለፉት መልእክት ለክልሉ ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት የመንግስትን ተግባራዊ ጥረት ያሳየ ነው ብለዋል።

ከዚህ በመነሳት የትግራይ ህዝብና በተለይም ወጣቱ ጦርነትን በመቃወም ለሰላምና ልማት በመትጋት የመንግስትን ጥረት መደገፍና ማገዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው የትግራይ ወጣቶች የስልጣን ባለቤት እንዲሆኑና በአሮጌ አስተሳሰብ ለጦርነት ከሚገፋፏቸው አካላት ራሳቸውን እንዲጠብቁ መምከራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም