ቀጥታ፡

የሆስፒታሎች ጥምረት የአገልግሎት ጥራትንና ትስስርን በማጠናከር የተገልጋዮችን እርካታ ማሳደግ አስችሏል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት መርሃግብር የሆስፒታሎችን ትስስር በማጠናከር የተገልጋዮች እርካታን ማሳደግ እያስቻለ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ። 

በታዳሽ ኃይል የታገዘ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት የሽልማት ስነ-ስርዓት  እንዲሁም የአምስተኛ ዙር የሆስፒታሎች ጥምረት የትኩረት አቅጣጫ ማስተዋወቂያ እና ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ይገኛል። 

በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት፤ መንግስት የጤና ዘርፉን ጥራት ያለው፣ ፍትሃዊና ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል። 

በተለይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኃላ የድንገተኛ ህክምናና ፅኑ ህሙማን ህክምና ላይ መሻሻል መምጣቱን ገልፀው፤ የግል ጤና ተቋማት ቁጥር በሶስት እጥፍ ማደጉን ተናግረዋል። 

ለ70 ዓመታት ያህል በአንድ አምራች ሲቀርብ የነበረው የኦክሲጅን ምርት በኮቪድ ወቅት 3 እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ 64 የኦክሲጅን ፕላንት መኖሩን ገልፀዋል።

የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅራቢዎች ቁጥር ማደጉንና የህክምና ግብዓትና መድኃኒት ስርጭትም መሻሻል እያሳየ መሆኑን አስረድተዋል። 

ከ5ሺህ በላይ የጤና ተቋማት ውል ወደተገባለት የመድኃኒት አቅርቦት ስርዓት መግባታቸውን ጠቅሰው፤ የእናቶችና ህፃናት ሞትም እየቀነሰ መምጣቱን ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት መርሃግብር የሆስፒታሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻልና የተገልጋዮች እርካታን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል። 

መርሃግብሩ በጤና ተቋማት መካከል ያለውን የእርስ በርስ ትብብር ማጠናከር ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተገልጋይ እርካታ አሁን ላይ 85 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል። 

አራተኛው ዙር መርሃግብር በመረጃ ላይ የተደገፈ የህክምና አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንደነበር አውስተው፤ ከዚህ ቀደም የተተገበሩ አራቱም ዙሮች ክፍተቶችን ማሟላት ላይ ያተኮሩ እንደነበርም አንስተዋል። 

አምስተኛው ዙር የተሟላ ህክምና አገልግሎት ላይ በማተኮር የተጀመሩ ማሻሻያዎችን ማጠናከር የሚያስችልና የሰው ኃይል ልማት ላይ አተኩሮ የሚተገበር እንደሚሆንም ጠቁመዋል። 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ጤናማና አምራች ዜጋ ለሀገር ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። 

ለጤናው ዘርፍ ከተሰጡት ተልዕኮ አንዱ ጥራት ያለው አገልግሎት በፍትሃዊነት ማዳረስ መሆኑን አንስተው ለዚህም ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት መርሃግብር በሆስፒታሎች መካከል ጤናማ ውድድር እንዲኖር በማድረግ የአገልግሎት መሻሻል እንዲመጣ እያስቻለ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም