ቀጥታ፡

በታዳሽ ኃይል የታገዘ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል  

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ በታዳሽ ኃይል የታገዘ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚከናወኑ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ ገለጹ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ለ380 ጤና ተቋማት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች እንዲሁም ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውሉ ከፀሐይ ብርሃን ኃይል የሚያመነጩ ግብዓቶችን ርክክብ አድርጓል። 


 

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የሁሉም ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የዩኒሴፍ (UNICEF) ተወካዮች፣ የአጋር ድርጅቶችና የኤምባሲ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ እንደገለጹት፤ ጥራቱን የጠበቀና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው። 

በታዳሽ ኃይል የታገዘ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡   

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ በሚሰጥባቸው ተቋማት በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የሚከሰተውን መስተጓጎል ለማስቀረት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሥራው ኢትዮጵያ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን ለማስፋፋት ከያዘችው አገራዊ ግብ ጋር የተጣጣመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ጥራቱን የጠበቀ፣ ፍትሐዊና ዘላቂ የጤና አገልግሎት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው የታዳሽ ኃይል የጤና ተቋማት አገልግሎታቸውን ያለ ኃይል መቆራረጥ እንዲሰጡ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል።

ይህ የታዳሽ ኃይል ግብዓቶች ስርጭት የጤና ተቋማቱን የኃይል ፍላጎት ከመሸፈን ባለፈ በአካባቢው የሚገኘው ማኅበረሰብም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል የሚያመቻች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ውስን በሆነባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ይበልጥ ለማዘመን ታቅዶ እየተሰራ ነው። 


 

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለይ የክትባት ማከማቻ ሥርዓትን ለማጠናከር እና አስተማማኝ የወሊድ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የኃይል አማራጮች ለሚያስፈልጓቸው ተቋማት ቅድሚያ ለመስጠት መለየቱንም ጠቁመዋል፡፡  

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ ( ዶ/ር) ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ሀይል ሀብት ያላት አገር መሆኗን አንስተው የዛሬው ግብአት አቅርቦትም ከአገር አቀፍ ኤሌክትሪፍኬሽን ፕሮግራም ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል።


 

በጤና ተቋማት የሀይል አማራጮችን ተደራሽነትና ዘላቂነት ለማጠናከር የሚሰሩ ስራዎችም በጋራ መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።

የዩኒሴፍ ተወካይ አቡበከር ካምፖ ኢትዮጵያ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በአፍሪካ እጅግ ታላቅ ከሆኑ የታዳሽ ኃይል የጤና ፕሮግራሞች አንዱን እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል።


 

በዛሬው እለት የተደረገው የግብአት አቅርቦትም በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና ለአካባቢ ጥበቃም ጉልህ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም