በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ሀሳብ ያለው ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ሀሳብ ያለው ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ነዋሪዎች
ጅግጅጋ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ለሀገሪቱ ዕድገትና ለህዝቦች ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከነገ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚጀምር ማስታወቁ ይታወሳል
ለመራጭነት የሚያበቃንን ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች፤ በመጪው ግንቦት 24 በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጠት የሚችሉበትን ካርድ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብና ለሀገር ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ጀማል ኢብራሂም፤ በአምስት ዓመት አንዴ የሚካሄደው ምርጫ ዜጎች ለሀገርና ህዝብ ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ የሚመርጡበትን ዕድል የሚያመቻች መሆኑን ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለው ሠላምና ፀጥታ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ምርጫዎች በተሻለ መልኩ ለመሳተፍና ድምጽ ለመስጠት ሰፊ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው፤ ይህንን ተጠቅመው በንቃት እንደሚሳተፉም አረጋግጠዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ መሀመድ ዑመር በበኩላቸው፤ ጠቅላላ ምርጫው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማፋጠንና ለሀገር ዕድገት የሚረዳ ወሳኝ ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል። ለሀገር ይጠቅማል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በጠቅላላ ምርጫው ለመራጭነት የደረሱ ዜጎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸውም አክለዋል።
ምርጫ የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ፈርሃን ሙሀመድ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ናቸው።
ካርድ በመውሰድ ለሀገር ዕድገት ይሰራል፤ የዜጎችን ህይወት ይለውጣል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።