ቀጥታ፡

ለመራጭነት የሚያበቃንን ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል 

ሀዋሳ/ቦንጋ/ሰመራ/አምቦ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች ገለጹ።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተናል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳዎችን ከማስቀመጥ ጀምሮ  የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወነ ነው።

ከነገ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ የሚጀመር በመሆኑም ኢዜአ የመራጮችን ዝግጅትን አስመልክቶ በተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

የቦንጋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ነስረዲን ሀሰን፤ በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሔደው ምርጫ ተመዝግበው ካርድ ለመውሰድና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም  እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዋል።


 

''በግሌም ይሁን ለአካባቢያችን እና ለሀገር የሚበጅ ፓርቲ በመምረጥ ሂደት የእኔ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ስለምረዳ ለመምረጥ የሚያበቃኝን ካርድ ለመውሰድ ተዘጋጅቻለሁ'' ነው ያሉት።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ እናኑ ከተማ፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚዲያ ስለፕሮግራማቸው የሚያስተላልፉትን ሀሳብ በመከታተል ይበጀኛል ያሉትን ለመምረጥ ከወዲሁ እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጁ ሆነው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ እናኑ ለእኔም ሆነ ለሀገር ይበጃል የምለውን ፓርቲ እመርጣለሁ ብለዋል፡፡

በዘንድሮው ምርጫ በድምጻቸው የሚበጃቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የመራጮች ምዝገባ ቀንን እየተጠባበቁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሠመራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሐዋ አብዱ ናቸው።


 

በተለይም ሴቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በመራጭነት በመሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አስረድተዋል።


 

በምዕራብ ሸዋ ዞን የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ቢንያም አሸቱ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ካርድ ለመውሰድ የምዝገባውን መጀመር እየተጠባበቀ መሆኑን ነው የተናገረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም