በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ የምርጫ ካርዳቸውን በወቅቱ በመያዝ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች እና ሴቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሆኖ እንዲካሄድ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል
በዚህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን፤ ሌሎች አስፈላጊ የምርጫ ቅድመ ዝግጅት ስራዎችንም እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተጨማሪም፣ በቦርዱ መርሀ ግብር መሠረት የመራጮች ምዝገባ ሂደት ነገ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች እና ሴቶች ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወጣት ማርቆስ እሸቱ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች ላይ በመሳተፍ እንደ ዜጋ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የሚጠበቅበትን መወጣቱን ተናግሯል።
ዘንድሮ የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ካለፉት ጊዜያት በተሻለ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ነው የተናገረው።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ዘሀራ በርጋ፤ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግና የምሰጠው ድምጽ ዋጋ እንደሚኖረው በማወቅ ይበጀኛል የምለውን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።
በተለይም ሁሉም ወጣት ይበጀኛል ወይም ተጠቃሚነቴን ያረጋግጥልኛል የሚለውን ፓርቲ መምረጥ እንዳለበት ገልጻለች፡፡
ወጣት አህመድ አሊ በበኩሉ፤ ወጣቱ ምርጫ ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ዕድገት ያለውን ጉልህ ፋይዳ በሚገባ ሊገነዘብ እንደሚገባ አንስቷል።
የዴሞክራሲ ባህላችን ሊያድግ የሚችለው በወጣቶች ተሳትፎ ነው ሲልም ጨምሮ ተናግሯል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የውብዳር ተመስገን፤ ምርጫ ተጠቃሚነትታችንን የምናረጋግጥበት መንገድ በመሆኑ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።
መምረጥ ሕገ-መንግስታዊ መብት መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንን ዕድል በመጠቀም ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ የገለፀው ደግሞ ወጣት ዮሴፍ አበራ ነው።
የመምረጥ መብቱን ለማረጋገጥም የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሀላፊ ሙህዲን ናስር ፌዴሬሽኑ ቀደም ባሉት ምርጫዎች ወጣቱን በማንቃት ረገድ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስታውሰዋል።
ዘንድሮ የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በተለያዩ አማራጮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡