ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የህዝብ ባህል፣ ታሪክና እሴት ላይ ዘርፈ ብዙ ምርምሮችን እያከናወነ ነው

አዳማ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የህዝብ ባህል፣ ታሪክና እሴት ላይ ዘርፈ ብዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት እንደገለጹት፤ ተቋሙ በኦሮሞ ባህል፣ እሴት፣ ስነ-ጥበብ፣ ታሪክ፣ ቋንቋና እድገት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። 

ወጣቶች መልካም ስብዕናን ተላብሰው ለሀገር ልማት እና እድገት እንዲተጉ የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል

ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ እና በክልሉ ከሚገኙ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከቱሪዝም ኮሚሽን፣ ከባህል ጥናት ማዕከል እንዲሁም ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ እስካሁን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከ70 በላይ የምርምር ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። 

ከእነዚህም መካከል በታሪክ፣ በቋንቋና በባህል ላይ ያተኮሩ ከ30 በላይ መጻሕፍት ታትመው ለማህበረሰቡ ተደራሽ ሆነዋል ብለዋል።


 

እነዚህ ስራዎች በተለይም የወጣቶችን የማንበብ ባህል ለማጠናከርና ሁለንተናዊ ስብዕናቸው እንዲገነባ ለማስቻል ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም አመልክተዋል።

የጥናት ውጤቶቹንና የመጻሕፍት ዝግጅቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች፣ ስራው በትውልዱ ላይ የሚታየውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት እንደሚረዳ ገልጸዋል።


 

ወጣት ስራጅ አህመድ እንደገለጸው፣ ንባብ ወጣቶች ስለ ማህበረሰቡ ስብዕናና ባህል እንዲያውቁ ያደርጋል። 

የገዳ ስርዓት መሰረታችንና ማንነታችን ነው ያለው ወጣት ስራጅ፣ ስለ ስርዓቱና ስለ ኦሮሞ እሴቶች በቂ እውቀት ለማግኘት የንባብ ባህላችንን ማጎልበት ይገባናል ብሏል። 

ተተኪው ትውልድ ስራን ከመናቅ ወጥቶ በልማት ስራዎች ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለበትም ነው የገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም