ወጣቶች መልካም ስብዕናን ተላብሰው ለሀገር ልማት እና እድገት እንዲተጉ የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች መልካም ስብዕናን ተላብሰው ለሀገር ልማት እና እድገት እንዲተጉ የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል
አሰላ፤የካቲት 26/2018 (ኢዜአ) ፦ በኦሮሚያ ክልል ወጣቱ መልካም ስብዕናን ተላብሶ ለሀገር ልማት እና እድገት እንዲተጋ የባለድርሻ አካላት ሚናን ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
የንባብና የሥራ ባህልን ለማጎልበት ያለመው 5ኛው የኦሮሚያ ወጣቶች ኮንፈረንስ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲንብሩ በኮንፈረንሱ ላይ እንደገለጹት፤ ወጣቱ የሕዝቡን ባህልና እሴት በአግባቡ ተረድቶ ለሀገር ግንባታ እንዲጠቀምበት የክልሉ መንግስት የባህል ተሃድሶ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ነጣጣይ ትርክትን በማስተካከል ወጣቶች መልካም ስብዕናን እንዲላበሱ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም የወጣቶችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም በማሳደግ ለሥራ ባህል ለውጥ ትኩረት እንዲሰጡ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተው በተለይ የስራ እድል ለማግኝት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
ለዚህም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያ በበኩላቸው፣ ወጣቶች በስነ-ምግባር ታንጸው ድህነትን ለመታገል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የክልሉ ወጣቶች የንባብ ባህላቸው እንዲያድግ እንዲሁም የስራ ባህላቸው እንዲለወጥ ተከታታይነት ያላቸው ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አሰራት፤ ኢንስቲትዩቱ የወጣቶችን አቅም ለማጎልበት ከአርሲ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች "ከጥናትና ምርምር ባለፈ በየአካባቢው የሥራ ባህላቸውን የሚያጎለብቱ አጫጭር የሙያና የክህሎት ስልጠናዎችን እየሰጠን እንገኛለን" ብለዋል።
የወጣቱ የሥራ ባህል ተለውጦ ውጤት ለማምጣት የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ያነሱት ደግሞ የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ከድር ናቸው።
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍቃዱ ምትኩ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በባህልና ማንነት ዙሪያ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።