ቀጥታ፡

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሆኖ እንዲካሄድ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሆኖ እንዲካሄድ አዋጅን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡   

የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም የምርጫ ቦርድን የምርጫ አስተዳደር አቅም በመገንባት ጤናማ የፖለቲካ ፉክክር እንዲፈጠር እያደረገ ነው

"የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ!" በሚል መሪ ሀሳብ በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 


 

መድረኩ በዋናነት በሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት እና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ተቋማት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት በቀጣይ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ በሚያረጋግጡባቸው ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መክሯል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ የተከናወኑ መሠረታዊ የለውጥ እርምጃዎች የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን በማሻሻል፣ ቦርዱ ያለምንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት እንዲሠራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል። 

መንግሥት ተቋሙ በሰው ኃይልና በሎጂስቲክስ እንዲደራጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህም ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን ምቹ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግና በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በቦርዱ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ገለልተኝነትን በማረጋገጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ማድረጋቸውን አፈ-ጉባኤው በአፅንኦት ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ቦርዱ ወደ ዲጂታል አሠራር እያደረገ ያለው ሽግግር የምርጫውን ተዓማኒነት ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።  

የምርጫ ዕጩዎች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መንገድ መከናወኑን ጠቁመው፤ የመራጮች ምዝገባም በዲጂታል ጣቢያዎች፣ በራሳቸው ስልክ መተግበሪያ አማካኝነት እንዲሁም በአካል ምርጫ ጣቢያ በመገኘት መመዝገብ የሚችሉበት ሥርዓት መዘረጋቱንም ተናግረዋል፡፡

የምርጫው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንቦችን አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

ለዚህም ለፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

የምርጫው ሂደት ነፃ፣ ፍትሐዊና አካታች እንዲሆን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም