ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ ወቅት ከ208 ሺህ 602 ሄክታር በላይ መሬት ይለማል 

ወልቂጤ ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከ208 ሺህ 602 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በጉጂ ዞን የቡና ልማትን ለማስፋፋት ከ70 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዓለምይርጋ ወልደስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች የሰብል ልማት ሥራ ተጀምሯል።

በበልግ ወቅት በክልሉ 208 ሺህ 602 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደተግባር  መገባቱንም ተናግረዋል።

በበልግ ለማልማት ከታቀደው መሬት 115 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥ 20 ሺህ 338  ሄክታሩ በበቆሎ፣ በድንች፣ በተለያዩ ሰብሎችና አትክልቶች እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በበልግ ከሚለማው አጠቃላይ መሬትም 32 ሚሊዮን 451 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የገለጹት ሃላፊው፣ በልማቱም ከ400 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ በበልግ ወቅት የሚጥለውን ዝናብ በእርሻ ማሳቸው ውስጥ ለማስቀረት የውሃ እቀባ ሥራ እንዲያከናውኑ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል። 

በሚቲዎሮሎጂ ትንበያ መሠረት የዝናብ ሁኔታው እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ ዓለምይርጋ፣ አርሶ አደሩም የተገኘውን እርጥበት በመጠቀም የእርሻና የዘር ሥራውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ  ሃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ  በበኩላቸው፤በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ከ82 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ እርሻ በበቆሎ፣ ድንች እና ሌሎችም ሰብሎች በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡


 

ምርታማነትን ለማሳደግም ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ከማቅረብ ባለፈ የግብርና ባለሙያዎች ተገቢውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በስልጤ ዞን ሚቶ ወረዳ ኤደነባ አጋዎ ቀበሌው አርሶ አደር ዋበላ ኑሪ፤ የበልግ ዝናብ በአካባቢያቸው እየጣለ መሆኑንና ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በበቆሎ ዘር ለመሸፈን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ።


 

ለምርት ወቅቱ የሚሆን ግብዓት በመንግስት ቀድሞ እንደቀረበላቸውና በባለሙያ ድጋፍም ታግዘው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በተገቢው በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት የማሳ ዝግጅት እያካሄዱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ የጣጤሳ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኑ አንሳ ናቸው ፡፡


 

አካባቢያቸው ለበልግ እርሻ የተመቸ የአየር ጸባይ ያለው በመሆኑ ከሚያለሙት 2 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም