ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን የቡና ልማትን ለማስፋፋት ከ70 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል

ነገሌ ቦረና፤ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፡- በጉጂ ዞን የቡና ልማትን ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ከ70 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የቡናና ሻይ ልማት ባለሙያ አቶ ብርሀኑ ፈይሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዘንድሮው ዓመት የዞኑን የቡና ልማት ለማስፋፋት የሚያስችሉ ከ61 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

ባለፉት ሰባት ወራትም ከ70 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ከእቅድ በላይ መፈፀም መቻሉን አብራርተዋል።

የተዘጋጁት ችግኞች በመጪው የክረምት ወቅት የሚተከሉ ሲሆን የተሻሻሉና የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ  መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎቹ በአብዛኛው ከጅማ ግብርና ምርምር እና ከይርጋለም አወዳ የምርምር ጣቢያ የተለቀቁ ሲሆን  በሄክታር ከ12 እስከ 15 ኩንታል ምርት ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።፡

ዝርያው ብርድና በሽታን በመቋቋም በቅርብ ዓመታት ምርት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም በምርምር ማዕከላቱ መረጋገጡን ነው የገለጹት፡፡

የቡና ልማቱን በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለማስፋፋት 10 ሺህ 500 ሄክታር አጠቃላይ መሬት መዘጋጀቱን አመልክተው የተሻሻለውን የቡና ዝርያ ለ61 ሺህ አምራች አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዞኑ በ12 ወረዳዎችና በ157 ቀበሌዎች ከ177 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት መሸፈኑንም ገልጸዋል።

በዞኑ ከሰብል ልማት እና ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን ከ108 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት ስራ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም