ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው

ባህር ዳር ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገራት ቱሪስቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለፀ።

በአማራ ክልል የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስታት፣ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች በርካታ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ።

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በገበታ ለሃገርና ለትውልድ ኢኒሼቲቭ የተገነቡ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትና የሎጎ ሃይቅ ሪዞርት ፕሮጀክቶች ለክልሉ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ እየሆኑ ይገኛል።

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋየ ከኢትዮጰያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የለውጡ መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው ዋና ዋና ዘርፎች መካከል  ቱሪዝም አንዱ ነው።

ዘርፉ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ ሆኖ እንዲዘልቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤታማ በመሆናቸው  በክልሉ የጎብኝዎች ቁጥርም ሆነ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እያደገ እንዲመጣ አድርጓል ብለዋል።

ባለፉት ሰባት ወራትም ከ10 ሚሊዮን 124 ሺህ የሚበልጡ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የተለያዩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል ነው ያሉት።

በዚሁ ወቅት ከዘርፉ  7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ያሉት ኃላፊው የጎብኝዎቹ ቁጥርም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ጊዜም  ከ29 ሺህ 900 የሚበልጡ የውጭ ሃገራት ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመትም የጎብኚዎች ቁጥርም ሆነ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በእጅጉ ማደጉን ጠቅሰው፤ ለዚህም በክልሉ የሰፈነው ሰላም የጎላ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል።

በቱሪዝም መስክ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅንጅት ለመስራት በመቻሉም የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም እያስቻለ መሆኑን  ገልፀዋል።

በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለውን ሚና የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም