ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ዱራሜ ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል

ርዕሰ መስተዳድሩ በከምባታ ዞን በሀምበሪቾ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ለሚገነባው "የኢትዮጵያውያን መንደር ፕሮጀክት" ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረተ ድንጋይ አኑረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የአድዋ አርበኞች ሀውልትን፣ 30 ጎጆዎችን፣ የህፃናት መጫወቻና መማሪያ ክፍሎችን፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ መዝናኛዎችን ያካተተ ሆኖ ግንባታው እንደሚከናወንም ተጠቁሟል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

ቀደምት አባቶች ነፃነቷን አስጠብቀው ባቆዩልን ሀገር አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የወቅቱ ትውልድ ኃላፊነት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡


 

የ"ሀምበሪቾ የኢትዮጵያውያን መንደር ፕሮጀክት" ሁሉንም ዜጎች የሚያሰባስብ ከመሆኑም በተጨማሪ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ከክልል አልፎ ለሀገር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የጢያ ትክል ድንጋይ የቱሪስት መዳረሻን ጨምሮ የሀምበሪቾ የኢትዮጵያውያን መንደርን በታቀደለት ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በበኩላቸው የ"ሀምበሪቾ የኢትዮጵያውያን መንደር ፕሮጀክት" በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረ የልማት ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የሀምበሪቾ ኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ በጎብኚዎች ዘንድ ያለው ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻውን በሚመጥን መልኩ በህብረተሰቡ ተሳትፎ በትብብር ለማልማት የሀብት ማሰባሰብ ስራ ስለመጀመሩም አስረድተዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያውያን መንደር ፕሮጀክቱን የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ህዝቦችን ባህል፣ ታሪክና እሴት በሚገልጽ መልኩ እንደሚለማ ገልጸዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ እውን መሆን አስተዳደሩና የአካባቢው ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡ 

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልልና የዞኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአካባቢው ተወላጆችና የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም