ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ሀገራት ለዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፡-የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አስከፊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ሀገራት ለዓለም አቀፍ ስምምነትና ቃል ኪዳኖች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የ‎ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ገለጸ።

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ የግብርና ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባቸዋል

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ዓለም አቀፍ ስምምነትና ቃልኪዳኖች ተፈፃሚነት ያላት ቁርጠኝነት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንዳስቻላት በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ተቋማዊ ልማት አማካሪ መንሱር ደሴ ገልጸዋል።

ከየካቲት 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የ‎ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ‎የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የአውደ ጥናት የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በአውደ ጥናቱ ማጠናቀቂያ ላይ ‎የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የአፍሪካ አስተባባሪ ጆንኪ ቴኑ፤ የአካባቢና የሥነ-ምኅዳር ደኅነንት ለማስጠበቅ ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።



 

አውደ ጥናቱም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ተግባራዊ የተደረጉ መርሃ ግብሮችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ስኬታማ የልምድ ልውውጥና ግብዓት እንደተገኘበት ገልጸዋል።

በፖሊሲዎችና የትኩረት መስኮች የተደረገው ውይይትም የዕውቀት ሽግግር የተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።

‎ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የመንግሥታቱን ድርጅት የአየር ንብረት ስምምነት መነሻ በማድረግ ለተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እያቀረበ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሀገራትም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አስከፊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ስምምነትና ቃልኪዳኖች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።


 

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአየር ንብረት ተቋማዊ ልማት አማካሪ መንሱር ደሴ በበኩላቸው፤ በአውደ ጥናቱ ከ14 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 150 ሙያተኞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ዓለም አቀፍ ስምምነትና ቃልኪዳኖች ትግበራ ያላት ቁርጠኝነት በልማት አቅጣጫዎቿ ላይ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።

በአውደ ጥናቱም ኢትዮጵያ በ‎ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም በተደረገ ድጋፍ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት መቅረባቸውን ተናግረዋል።

ከሀምሌ ወር ጀምሮ ለአራት ዓመታት የሚተገበረው ‎የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም መርሃ ግብርም ከኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫዎች ጋር ተጣጥመው እንደሚተገበሩ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም