በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከእጣንና ሙጫ ምርት ሽያጭ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከእጣንና ሙጫ ምርት ሽያጭ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ትኩረት ተደርጓል
ገንዳውኃ፤ ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ጎንደር ዞን ከእጣንና ሙጫ ምርት ሽያጭ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ትኩረት መደረጉን የዞኑ ደን ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በአማራ ክልል ከሚመረቱ ገበያ ተኮር ምርቶች መካከል የተፈጥሮ እጣንና ሙጫ በዋነኝነት የሚጠቀስ ሲሆን ከአንድ የሙጫ ዛፍ በዓመት እስከ 30 ኩንታል የእጣን ምርት ይገኛል።
በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በውስጥ አቅም ለመሸፈን በመቻሉ ለበልግ እርሻ ምቹ ሁኔታን ተፈጥሯል
በጽህፈት ቤቱ የአካባቢ የሕግ ተከባሪነትና የማኅበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አድጎ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በዞኑ የተፈጥሮ እጣንና ሙጫ ደን ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዞኑ በሚገኘው ከ334 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የእጣንና ሙጫ ደን ላይ 41 ማህበራትና ባለሃብቶችን በማሰማራት የማምረት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱም ከአምስት ሺህ ኩንታል በላይ የእጣንና ሙጫ ምርት በማምረት ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከሚገኘው ገቢም ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው በሮያሊቲ ገቢ የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከአንድ ሺህ 125 ኩንታል በላይ እጣንና ሙጫ ማምረት መቻሉን ጠቁመው ከዚህም ለመንግስት በሮያሊቲ ክፍያ አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማስገባት መቻሉን አስረድተዋል።
በዞኑ መተማ ወረዳ ለምለም ተራራ ቀበሌ በተፈጥሮ ሀብት ህብረት ስራ ማህበር ተደራጅተው እጣንና ሙጫ በማምረት ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ኑሬ አዳነ እንዳለው፤ የተፈጥሮ ሀብቱን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ ነው።
አስራ አንድ አባላት ያሉት ማህበር በመመስረት ከ100 ኩንታል በላይ የእጣን ምርት አምርተው በመሸጥ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግሯል።
"የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ በመጠበቅ ሀብት እያፈራን ነው" ሲል ነው የገለጸው፡።
በመተማ ወረዳ የለምለም ተራራ ቀበሌ ነዋሪው ጥላሁን ዋሴ በበኩሉ፤ ባለፈው ዓመት ከመቶ ኩንታል በላይ ምርት ያገኙ መሆኑን አስታውሶ፤ በዚህ ዓመት ከአምናው የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚችሉ አስረድቷል።
ባለፈው ዓመት በአካባቢው የተመረተውን የእጣንና ሙጫ ምርት በመሸጥ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።