ቀጥታ፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ሚና አጠናክረው መቀጠል አለባቸው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያስላሴ ገለጹ፡፡ 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው

አምስተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት "ራስን መቻል ለዘላቂ ሰላምና አካታች ልማት " በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል።

በመክፈቻ መርኃግብሩ  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርዓያስላሴ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎች  በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል፡፡

ይህም የሆነው መንግሥት የዜጎችን የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ የህግና የአሰራር የአዋጅ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ ነው ብለዋል።

ሲቪል ማኅበራት አካታች ሀገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትህ ሂደት እና ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ  ጉዳዮች ላይ የማይተካ ሚና እንዳላቸው አፅንዖት ሰጥተዋል። 

እነዚህ ኹነቶች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለዘላቂ ሰላም ያላቸው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ ድርጅቶቹ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ሲቪል ማኅበራት አሠራራቸውን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ መመሥረት እንዳለባቸው ሚኒስትሯ አሳስበዋል። 


 

የጋራ ቤታችን የሆነችውን ሀገር ለማፅናት የተናበበ ጥረታችን ሊጠናከር  ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ መንግሥት ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ዛሬ የሚገነባው ሰላምና ልማት ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት በመሆኑ መንግሥት ከሲቪል ማኅበራት ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ኤግዚቢሽኑ ከዛሬ የካቲት 26 እስከ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም