የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተኩ ስትራቴጂያዊ አጋሮቻችን ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
5ኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ኤግዚቢሽን በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል ተከፍቷል።
ሪፎርሙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን ሚና አጎልብቷል
በመክፈቻ መርኃግብሩ የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርዓያስላሴ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በዚህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተኩ ስትራቴጂያዊ አጋሮቻችን ናቸው ብለዋል።
በመንግሥትና በግል ዘርፍ የማይሸፈኑ ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን በመሙላት ለኢኮኖሚ ብልፅግና መረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላችሁ የልማት አጋሮች ናችሁ የሚል ጽኑ እምነት ይዞ እየሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የትውልድና ማኅበራዊ ትስስር ገንቢዎች በመሆናቸው ትውልድን በመቅረጽ፣ በዜጎች መካከል መተማመንን በመገንባትና ማኅበራዊ ትስስራችንን በማጠናከር ረገድ የላቀ ሚና አላችሁ ብሎ መንግሥት ያምናል ሲሉም አክለዋል።
እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች ወደ ተግባር ለመለወጥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በዚህም ዘርፉን እጅግ ገዳቢ የነበረውን አዋጅ በመሻር የመደራጀት መብትን በሙሉ ሁኔታ የሚያረጋግጠው አዋጅ ቁጥር 1113/2011 እንዲጸድቅ መደረጉ ዋናው ስኬት ነው ብለዋል።
እነዚህ የሕግ ማሻሻያዎች ያለ አግባብ ተጥለው የነበሩትን የፋይናንስና የአስተዳደር እንዲሁም በሌሎች መስክ የነበሩ ገደቦችን በማንሳት የሲቪክ ምኅዳሩን ማስፋቱን ተናግረዋል፡፡
ተቋማዊ ሪፎርም በውጤታማነት መተግበሩን ተከትሎ የአገልግሎት አሰጣጡ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን በመደረጉ በመርህ ላይ የተመሠረተ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ምቹ አውድ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም መንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል የቅንጅትና ትብብር ማዕቀፍ ተዘጋጅቶና ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ መድረኮች ተደራጅተው ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩና አስተዋጿቸው ማደጉን ተናግረው በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ወደ ሦስት እጥፍ ገደማ አድጎ በሀገር ደረጃ ከ 8 ሺህ 410 በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።
በውጤቱም የሲቪል ማህበራት በልማት፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ሰላም እሴት ግንባታ፣ በትውልድ ግንባታ፣ በሰብአዊ ድጋፍ እና በመሳሰሉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት አስተዳደር ታሪክ ውስጥ አሁን ያለንበትን ወቅት ወርቃማው ዘመን እንድንለው ያደርገናል ብለዋል።
በቀጣይ የሀገር ግንባታና የብልፅግና ጉዞን ለማፍጠን ለሀገራዊ መግባባት፣ ለዴሞክራሲ ባህልና ለጠነከረ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚናቸውን አጠናከረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ዴሞክራሲን የመትከልና የማጽናት ሀገራዊ ጥረት ለማሳካት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በመራጮች ትምህርትና በመታዘብ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀገር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት መደገፍ እና ከሀገራዊ አጀንዳዎች ጋር ራስን ማጣጣምና ተቋማዊ ተጠያቂነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ይህ ሳምንት ከመንግሥትና ከግል ዘርፉ ጋር ያላችሁን ስትራቴጂያዊ አጋርነት በማጠናከር በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላችሁን የማይተካ ሚና በቁርጠኝነት ለመወጣት የሚያስላችሁ ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።