ቀጥታ፡

ሪፎርሙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን ሚና አጎልብቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፦የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሪፎርም በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ላይ የድርጅቶቹን ሚና ማጎልበቱን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ገለጹ።

አምስተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ከየካቲት 26 ቀን 2018 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። 

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ ድርጅቶቹ በሀገረ መንግሥት ግንባታና በልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። 

ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው በሪፎርሙ አማካኝነት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል በመፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሚናቸው የጎላ ነው የሚል አስተሳሰብ ጎልብቷል ነው ያሉት።

በአምስተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ድርጅቶቹ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ በማስተዋወቅ ረገድ የሚኖረውን ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ ከነገ የካቲት 26 እስከ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል ብለዋል።

በሁነቱ ላይ ከዘርፉ ጋር በተያያዙ አጀንዳዎች ዙሪያ የፓናል ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፣ 123 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበት ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። 

እነዚህ የፓናል ውይይቶች የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ በመምከር ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለማመንጨት ያስችላሉ ብለዋል።

አክለውም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍና ከልማት አጋሮች ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ለሀገር እድገት በተሻለ ሁኔታ እንዲሰሩ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል። 

ህብረተሰቡ፣ ተቋማትና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በአምስተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ላይ በመገኘት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም