የአካባቢያችንን ሰላም በዘላቂነት በመጠበቅ የልማት ተሳትፏችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያችንን ሰላም በዘላቂነት በመጠበቅ የልማት ተሳትፏችንን እናጠናክራለን
ወልዲያና ባህር ዳር ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የአካባቢያችንን ሰላም በዘላቂነት በመጠበቅ የልማት ተሳትፏችንን እናጠናክራለን ሲሉ የባህር ዳር እና ወልዲያ ከተሞች የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።
የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የድርሻችንን እንወጣለን- የሐይማኖት አባቶችና የመንግስት ሰራተኞች
የወልዲያና የባህር ዳር ከተሞች አስተዳደሮች የመንግስት ሰራተኞች "ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛም እንሆናለን" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ውይይት አካሄደዋል።
በወልዲያ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት አቶ አሳዬ በላይነህ እንደገለጹት፤ ጸረ ሰላም ሀይሎችን በመመከት ድርሻቸውን ለማጠናከር ተዘጋጅተዋል።
የአካባቢን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ የአገርን እድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ በየተሰማራበት የሥራ መስክ መትጋት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ፈንታው አዲሱ በበኩላቸው አገራቸውን ክደው ከጠላት ጋር የሚያብሩ ኃይሎች ከባንዳነት ያለፈ ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው ብለዋል።
በአካባቢያቸው ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲፋጠን በአንድነት መቆም እንደሚገባም አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የወልዲያ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገብሬ፤ የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን ሴራ በመመከት አገርን ከነክብሯ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የመንግስት ሰራተኛው የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ግዛቸው፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን ገልፀዋል።
የመንግስት ሰራተኛው ሰላምን አፅንቶ ማስቀጠልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚሰሩ ስራዎች ውስጥ እየተወጣ ያለውን ሚና ማጠናከር አለበት ብለዋል።
በተጨማሪም የመንግስት ሰራተኛው በሰዓቱ በመገኘትና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የህዝብ ቅሬታዎችን ማስወገድ እንዳለበት አመልክተዋል።
በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አሁን ያለውን ሰላም አፅንቶ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።