የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የድርሻችንን እንወጣለን- የሐይማኖት አባቶችና የመንግስት ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የድርሻችንን እንወጣለን- የሐይማኖት አባቶችና የመንግስት ሰራተኞች
ደሴና ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ ሰላማችንን በማጽናትና አንድነትን በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የደሴና ደብረ ማርቆስ ከተሞች የሐይማኖት አባቶችና የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።
በአካባቢያችን ሰላምን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠል ቁርጠኞች ነን
በደሴና ደብረ ማርቆስ ከተሞች “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ የልማት አርበኛ እንሆናለን” በሚል መሪ ሀሳብ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከሐይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የደሴ ከተማ አስተዳደር ቤተ-ክህነት ስራ አስኪያጅ መላከ ብርሃን ኪሮስ ፋሲል እንደገለጹት፣ ከሌሎች እምነት ተቋማትና ተከታዮች ጋር በመቀናጀትና አንድነታችንን በማጠናከር ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል።
ቤተክርስቲያኗ ስለ ሰላም አብዝታ እያስተማረች እንደምትገኝ ጠቁመው፣ ይህም አሁን በአካባቢው ለሰፈነው ሰላም የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ሼህ ኢሳ በሪሁን በበኩላቸው፣ በከተማዋ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገለፀዋል።
መንግስት አሁንም የሰላም በሩን ክፍት በማድረግ ልዩነቶችን በንግግርና በውይይት ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፣ የሰላምን አማራጭ የማይቀበልን አካል እናወግዛለን ብለዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ በበኩላቸው፣ ህብረተሰቡን በማስተባበር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ በጋራ በመሆንና በየሰፈሩ በመደራጀት አካባቢውን በመጠበቅና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በመጠቆም ተባባሪነቱን ዳግም እንዲያረጋግጥም አስገንዝበዋል።
የደሴ ከተማ ከንቲባ የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ አቶ አሸናፊ አለማየሁ በበኩላቸው፣ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ሰላሙን ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ መክረዋል።
በተያያዘም በደብረ ማርቆስ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ ፤የመንግስት ሰራተኞች ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ ድርብ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የመንግስት ሰራተኛው በየተሰማራበት የስራ ዘርፍ ፈጣንና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል።
ይህም በከተማዋና አካባቢው ልማት እንዲረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው የመልካም አስተዳደር ችግር የሚስተዋልባቸው ተቋማትም ፈጥነው ሊያስተካክሉ ይገባል ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አዲሱ ብርሃኔ፤ በከተማዋ አሁን የተገኘውን ሰላም አጽንቶ ለማዝለቅ የመንግስት ሰራተኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ሰላምን ለማደፍረስ፣ ህዝብን ለማሰቃየትና ልማትን ለማስተጓጎል የተነሳን ማንኛውንም ሃይል ከመንግስት ጎን በመሆን ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በከተማችን እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ አያሌው ናቸው።
በደሴና ደብረ ማርቆስ ከተሞች በተካሄደው ውይይት ላይ የመንግስት ሰራተኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።