ቀጥታ፡

ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል 

ወልቂጤ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በተሰራው ሥራ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ባለፉት ሰባት ወራት 1 ሺህ 538 የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፓርኩን መጎብኘታቸውም ተመላክቷል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጠቅላላ የቆዳ ስፋቱ 360 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ይሸፍናል።

ብሔራዊ ፓርኩ በውስጡ በርካታ የዱር እንስሳት፣ ከ250 በላይ አዕዋፋት፣ የውሀ ውስጥ እንስሳት፣ ለእጣንና ለመድሃኒትነት አገልግሎት የሚውሉ ዛፎችና የተለያዩ ማዕድናትን በውስጡ አካቶ ይዟል።


 

በፓርኩ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች፣ ፍል ውሃ እና ዋሻ የሚገኝ ሲሆን የቱሪስት መስህብም ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መስፍን ተካ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ለፓርኩ ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ ከማድረግ ባለፈ የማስተዋወቅ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል።


 

የፓርኩን ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ስነ-ምህዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳውን ለማሳደግ እንዲሁም በፓርኩ ውስጥ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና የደን ጭፍጨፋን ለመግታትም እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ በፓርኩ የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ የተሰራ ሲሆን የማህበረሰብ ሎጅ ለመገንባትም የዲዛይን ሥራ ተጠናቋል።

ፓርኩን ከማልማትና ከመጠበቅ ባለፈ ለማስተዋወቅ በተሰራው ሥራ የጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን የጠቀሱት ሃላፊው ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ሰባት ወራት 1ሺህ 100 የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፓርኩን ሲጎበኙ ዘንድሮ ቁጥሩ ወደ 1ሺህ 538 ማደጉን ተናግረዋል።

የፓርኩ የዱር እንስሳት ጥበቃና እንክብካቤ ባለሙያ አቶ አበራ ጊቤ በበኩላቸው፤ በፓርኩ ተፈጥሯዊ መስህቦችን ከማልማት፣ ከመጠበቅና መንከባከብ በተጨማሪ የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለፓርኩ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ጥበቃ መደረጉ ብዝሃ ህይወትን ጠብቆ ለማቆየት እያስቻለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ስካውት አራጋው ካሳ ናቸው።

ህገወጥ ሰፈራና የደን ጭፍጨፋ በመቀነሱ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወንና ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ ማስቻሉንም ተናግረዋል።


 

ፖርኩን ሲጎበኙ ከነበሩት መካከል ወጣት ደስታ ጊዜያቱ በፓርኩ የተለያዩ አስደናቂና የተፈጥሮ መስህቦችን መመልከቱን ገልጿል።

የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በማዘጋጀትና ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም መስራት እንደሚገባም አመልክቷል።


 

ፓርኩ በብዝሃ ህይወት የታደለ መሆኑ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ምቹና ሳቢ እንዳደረገውም ነው ጎብኚዎቹ የገለጹት ።

በውስጡ ያሉ የተለያዩ እንስሳትና እጽዋትን መጠበቅን ጨምሮ ለፓርኩ ብዝሀ ሕይወት መጠበቅ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም