የሰሜኑ ጦርነት የተከሰተው ህወሓት ለውጥን ባለመቀበሉ እና ያረጀ እሳቤን የማስቀጠል አባዜ ምክንያት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሰሜኑ ጦርነት የተከሰተው ህወሓት ለውጥን ባለመቀበሉ እና ያረጀ እሳቤን የማስቀጠል አባዜ ምክንያት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018 (ኢዜአ)፦ የሰሜኑ ጦርነት የተከሰተው የህወሓት አመራር ለውጥን ባለመቀበሉ እና ያረጀ እሳቤ የማስቀጠል አባዜ ምክንያት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የሰሜኑ ጦርነት መነሻ ምክንያቶችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ህወሓት ለውጥን ባለመቀበሉ እና እኔ ብቻ በሚል ስሜት በመዋጡ ግጭት እንዲነሳ መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል።
ህወሓት ወደ መሬት መውረድ በማይችል ያረጀ አስተሳሰብ የታሠረ ድርጅት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ዓይኑን ጨፍኖ ራሱን ወደ አደጋ የሚከቱ ርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱንም ተናግረዋል።
የለውጡ ኃይል የጀመረውን ጉዞ ለማደናቀፍ መሞከሩን ገልጸው፤ በህወሓት ቆሞ ቀር አስተሳሰብ የተነሳው ጦርነት ጉዳት ማስከተሉንም አንስተዋል።
ሁለተኛው ቁልፍ ምክንያት ደግሞ ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጋር የተሣሠረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህወሓት ኢትዮጵያ በጥርጣሬና በሥጋት ውስጥ እንድትኖር መስራቱ ለችግሮች መባባስ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
ቆሞ ቀሩ ኃይል ከ50 ዓመት በፊት ከነበረው አስተሳሰብ ውጭ ሊንቀሳቀስ አለመቻሉን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ከለውጡ ጋር አብሮ ለመሄድ እንዳላስቻለው ገልጸዋል።
የለውጥ ኃይሉ ዓለምን ያስደመመ ተአምራዊ ለውጦችን ማምጣቱን ጠቅሰው፤ ቆሞ ቀር ኃይሉ ከለውጥ ኃይሉ ጋር ተስማምቶ ሕዝቡንና ነፍሱን እንደመለወጥ የልማት ሽታ ከማያውቁ ኋላቀሮች ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሀገር ደረጃ ያለው የፖለቲካ ስብራት ሌላኛው መንስኤ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተሳሳተ ትርክት ላይ የተመሰረተው ፖለቲካዊ መዋቅር የፖለቲካ ስርዓቱ እንዲበላሽ ማድረጉን ነው ያብራሩት።
ጦርነቱ የራሱ ልዩ ገጽታዎች እንዳሉት ሆኖ ከሀገራዊ መዋቅር ችግር የተለየ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም ብለዋል።
ይህ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሰበር አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይሄንን ለመስበር ደግሞ ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ ትውልድ ይበቃል ብለን መሥራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
የመንግስት አቋም ችግሮችን በውይይት መፍታት አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ በጽኑ እንደሚያምንም ገልጸዋል።
ይሄንን ለማድረግ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ወሳኝ ሀገራዊ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን ብለዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እስካሁን ከሞላ ጎደል ከትግራይ ውጭ አብዛኛው ሥራ እየተገባደደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልል ግን ውይይት እንዳይደረግ፣ ሕዝባችን ቁጭ ብሎ እንዳይወያይ፣ ጥያቄ አንሥቶ መፍትሔ እንዳያገኝ፣ ያ ቆሞ ቀር ኃይል ሆን ብሎ እየሠራ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ደግሞ ትክክለኛ አካሄድ ነው ብዬ አላምንም ብለዋል።