ቀጥታ፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ያደረጋቸው የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎች ውጤት አስገኝተዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሥራዎቹን በውጤታማነት ማከናወን የሚያስችሉ የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ገለጹ፡፡

"የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ!" በሚል መሪ ሀሳብ በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በፍርድ ቤቶች የዳኝነት ነፃነትን ያጠናከሩ እና የፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመን ያስቻሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል

መድረኩ በዋናነት በሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት እና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ተቋማት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት በቀጣይ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ በሚያረጋግጡባቸው ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መክሯል፡፡


 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፤ ተቋሙን ከወገንተኝነት የጸዳ፣ ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ ሰፊ የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ተቋሙን ነፃ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሕግ ደረጃ መሟላታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኦዲት ሽፋን ዕድገት በተመለከተም የፋይናንሻል ኦዲት ሽፋን መቶ በመቶ መከናወኑን ጠቅሰው የክዋኔ ኦዲት ደግሞ ከነበረበት 24 በመቶ ወደ 41 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከአካባቢያዊ ኦዲት እስከ መረጃ ሥርዓትና ልዩ ኦዲት ድረስ አዳዲስ ዘርፎች ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች የተቋሙ ተዓማኒነትና ጥራት መጨመሩን ጠቁመው በኦዲት ግኝቶች አማካኝነት በርካታ ገንዘቦችን ተመላሽ እንዲሆን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ተቋሙ የሀገርን ሀብት በማስጠበቅ ረገድ ያለውን ሚና በተግባር ያረጋገጠ መሆኑ ተመላክቷል።

ተቋሙ የቴክኖሎጂ ለውጡን ተከትሎ ሥራዎቹን ይበልጥ ለማዘመን በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የኦዲት አስተዳደርና የመረጃ ትንተና ሥርዓቶችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም በቀጣይነት ለመገንባት ራሱን የቻለ የሙያ ማበልጸጊያ ኢንስቲትዩት የማቋቋም ግብ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም