ቀጥታ፡

በፍርድ ቤቶች የዳኝነት ነፃነትን ያጠናከሩ እና የፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመን ያስቻሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ ዓመታት የዳኝነት ነፃነትን ያጠናከሩ፣ ግልጽነትን የፈጠሩና የፍትሕ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ ማዘመን ያስቻሉ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ገለጹ። 

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሆኖ እንዲካሄድ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል

"የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ!" በሚል መሪ ሀሳብ በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።  


 

መድረኩ በዋናነት በሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት እና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ተቋማት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት በቀጣይ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ በሚያረጋግጡባቸው ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መክሯል፡፡ 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፤ የፍርድ ቤቶች የለውጥ ተግባራትን አስመልክቶ ባቀረቡት የመነሻ ሐሳብ፤ የዳኝነት ነጻነትን ለማጠናከር የሕግ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ፍርድ ቤቶች ከሕግ ማሻሻያ ጀምሮ እስከ ሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ድረስ የሚዘልቁ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቶችን ተቋማዊ ነፃነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ የሕግና የአሠራር ለውጦች መደረጋቸውን ገልጸዋል። 

ከእነዚህም መካከል የፋይናንስ ነፃነትን ማረጋገጥ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች በራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ እንዲመሩ መደረጉና የዳኞች ምልመላ ሙሉ በሙሉ በብቃት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን መደረጉ በሪፎርሙ የተመዘገቡ ስኬቶች ናቸው ብለዋል፡፡ 

የሕዝብን አመኔታን ለመጨመር የግልጽ ችሎት ተደራሽነትን ከነበረበት 65 በመቶ ወደ 91 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡ 

የመዝገብ የመሻር ምጣኔን ለመቀነስ የድህረ-ውሳኔ ኦዲትና በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድ ያስመዘገቡት ውጤት አስደናቂ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድምፅን በቀጥታ ወደ ጽሁፍ የሚቀይር ቴክኖሎጂ በችሎቶች ጥቅም ላይ መዋል መጀመሩን ጠቁመዋል። 

በራስ አቅም የበለጸጉ የሬጅስትራርና የዳኞች ዳሽቦርዶች እንዲሁም የሰበር ውሳኔ መፈለጊያ ኢንዴክስ ሲስተሞች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ብቻ በእርቅ የተቋጩ መዝገቦች የገንዘብ መጠን ከ354 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱ የሥርዓቱን ውጤታማነት እንደሚያሳይም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የዳኝነት ነፃነትንና ተጠያቂነትን ይበልጥ ማላቅ፣ ተደራሽነትን ለማስፋት ተንቀሳቃሽ ችሎቶችን ማጠናከርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ወደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሠሩም ፕሬዚዳንቱ  አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም