ቀጥታ፡

የባቡር መስመር ዝርጋታው የሀገር በቀል የግንባታ አቅማችንን በተግባር ያሳየንበት ነው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦የኤ.ኤ.ም.ጂ ኢንዱስትሪ ፓርክ የባቡር መስመር ዝርጋታ የሀገር በቀል የግንባታ አቅማችንን በተግባር ያሳየንበት ነው ሲሉ በግንባታው የተሳተፉ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

‎ኢትዮጵያ በባቡር መሰረተ ልማት ዘርፍ የነበራትን የውጭ ድጋፍ ፍላጎት በሀገር በቀል እውቀትና ክህሎት በከፍተኛ ደረጃ እየተካች ትገኛለች። 

ሀዋሳ ከተማን ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - ከንቲባ ጥራቱ በየነ

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እየተገነባ ያለውና የኤ ኤም ጂ (AMG) ኢንዱስትሪ ፓርክን ከዋናው መስመር ጋር የሚያገናኘው የባቡር ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት መጠናቀቂያው ላይ ደርሷል። 

ይህ ስኬት ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን ቴክኒካዊ ብቃት በተግባር ያረጋገጠችበትና በራስ አቅም የመመራት ጉዞዋን ያፋጠነ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል።


 

በዲዛይን፣ በግንባታና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች እየተመራ ያለው ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት 87 በመቶ ደርሷል።

‎ለስድስት ወራት የታቀደውና የሦስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ሥራ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ቀድሞ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

‎በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ባለሙያዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በራስ አቅም እየተገነባ በሚገኝ ፕሮጀክት ላይ መሳተፋቸው ትልቅ ዕድል መሆኑን አንስተዋል።


 

‎‎የፕሮጀክቱ  ማናጀር ንግስት ሀይሉ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል። 

ቀደም ሲል የባቡር ግንባታዎች በቱርክና በቻይና ኩባንያዎች ይከናወኑ እንደነበር አንስተው፤ አሁን ግን በራሳችን አቅም መስራት አለብን በሚል ብሄራዊ ቁጭት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

‎የፕሮጀክቱ ስኬታማነት ለሀገሪቱ ትልቅ ልምድ ማስገኘቱን ገልጸው፣ የኢትዮጵያን የባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ሙሉ ዝግጁነትን ፈጥሯልም ነው ያሉት።

የፕሮጀክቱ የትራክ ወርክ ማናጀር ኦብሳ ጀማል በበኩላቸው፣ ግንባታው ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ያለ ምንም የውጭ ድጋፍ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ መከናወኑ ታላቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በስኬት መወጣት መቻላቸው ከፍተኛ በራስ መተማመን እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

ስራው በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች መከናወኑ በተለይም ለውጭ ኮንትራክተሮች ይከፈል የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረቱ ለሀገራችን ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።

የፕሮጀክቱ የመካኒካል ማናጀር ሮባ ጠኖ፣ ኢትዮጵያ በባቡር ቴክኖሎጂ ዘርፍ የነበራትን የውጭ ባለሙያዎች ጥገኝነት በሀገር በቀል እውቀት በመተካት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈቷን ገልጸዋል።


 

‎ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር በመሆኗ በርካታ የባቡር መሰረተ ልማቶች እንደሚያስፈልጓት የገለጹት ባለሙያው፣ ይህ ፕሮጀክት ለቀጣይ ሥራዎች ትልቅ መሠረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ መንግስት በሀገር ውስጥ አቅም ላይ በመተማመን ይህንን ዕድል በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በቀጣይም በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ውጤታማ ስራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም