ቀጥታ፡

ሀዋሳ ከተማን ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - ከንቲባ ጥራቱ በየነ

ሀዋሳ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦ ሀዋሳ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለፁ።

የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት 2ኛ ዙር 10ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 24ኛ መደበኝ ጉባኤውን አካሂዷል።

‎የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ከተማዋን በማዘመን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው።

‎በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በከተሞች የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ በሃዋሳም ተግባራዊ መደረጉ ከተማዋን ምቹ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።


 

በከተማዋ አመራሩን፣ ህብረተሰቡንና ባለሙያዎችን በማቀናጀት እየተካሔደ ያለው የኮሪደር ልማት ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም ከንቲባው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም 8 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ አዲስ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ጨምሮ የአረንጓዴ ስፍራዎች ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

‎የኮሪደር ልማቱ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የሕፃናት መጫዎቻዎች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ የታክሲ መጫኛና ማውረጃን ጨምሮ ተርሚናሎች እንዳሉትም አስረድተዋል።

ሕብረተሰቡ ለኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም ከ358 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የሚተመን ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

እንደከቲባው ገለጻ የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ከማስዋብ በተጨማሪ ለበርካታ ወጣቶችም ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ለመፍጠር አስችሏል።

በአረንጓዴ ልማትና በፅዳት ሥራም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ፅዳትና ውበትን በዘላቂነት ለመጠበቅ የተደረገው ጥረትም አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ገቢን በማሳደግ፣ የሥራ ባህልን በመቀየር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ባከናወናቸው ተግባራት እመርታ እንደታየም አመልክተዋል።

‎የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ደምሴ ዳንጊሶ በበኩላቸው፤ በኮሪደር ልማት ሥራዎች የታየው አፈፃፀም የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ አስችሏል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ በከተማዋ የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ዘላቂ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ከምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ዘላለም ላሌ፤ በከተማዋ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ለኢኮኖሚ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከሥራ ባህል መጎልበት አኳያም እየታየ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጹት።

መልካም አስተዳደርን ለማስፋነና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴን ከመከላከል አንፃር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም