በአካባቢያችን ሰላምን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠል ቁርጠኞች ነን - ኢዜአ አማርኛ
በአካባቢያችን ሰላምን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠል ቁርጠኞች ነን
ገንዳውኃ/ደብረ ብርሃን፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦በአካባቢያቸው ሰላምን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞንና በደብረብርሃን ከተማ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ገለጹ።
የኃይማኖት አባቶች በልማትና ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን የላቀ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግስት ሠራተኞች እና የደብረ ብርሃን ከተማ የሃገር ሽማግሌዎች "ለሰላም ዘብ እንቆማለን! የልማት አርበኞች እንሆናለን" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን በተካሄደው መድረክ ላይ ከተሳተፉት የመንግስት ሠራተኞች መካከል የዞኑ ውሀና ኢነርጂ መምሪያ ባለሙያ አቶ ግርማ ሺመላሽ እንደገለጹት፤ የአካባቢን ሰላም መጠበቅ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ሃላፊነት ነው።
"እኔም የአካባቢዬን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር በሙያዬ ህዝቡን በፍትሃዊነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ" ያሉት አቶ ግርማ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ለሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎችም ጆሮ እንደማይሰጡ ተናግረዋል።
አቶ ዘመነ ጥጋቡ የተባሉ የዞኑ ግብርና መምሪያ ባለሙያ በበኩላቸው፣ ሰላምን ማፅናት በግብርና ሙያ ምርታማነትን ከማሳደግ ሥራ ተለይቶ አይታይም ብለዋል።
ሰላምና ልማትን በማጠናከር የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ከሙያቸው ባሻገር ማህበረሰቡን በማስተባበር ለዘላቂ ሰላም ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለው ማሩ፤ የመንግስት ሠራተኞች ለሀገር ግንባታና ዘላቂ ሰላም መስፈን የላቀ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
በአካባቢው ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን ተከታታይነት ያለው ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ሰላም እየተረጋገጠ መምጣቱን ተናግረዋል።
የዞኑ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነጋ ከፋለ በበኩላቸው፤ የመንግስት ሠራተኛው በአገልጋይነት ስሜት ለሰላምና ልማት አርበኛ ሆኖ መገኘት አለበት ብለዋል።
በተያያዘ ዜና በደብረ ብርሃን ከተማ ከሀይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በሰላም፣ በልማትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ደረጀ ደርቤ እንደገለጹት፣ የፀጥታ ችግሩ በዘላቂነት ተፈቶ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።
በአካባቢያቸው ሰላም እንዲጸና አበክረው ከመስራት ባለፈ ለተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች እውን መሆን የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ የማነብርሃን ዝቄ፤ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ማህበረሰቡን በማስተባባር ስለሰላም ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ፡ ህብረተሰቡ በውጭ ጠላቶች ለሚጠነሰስ ሴራ ትኩረት ሳይሰጥ የአካባቢውን ሰላም ማጽናት እንዳለበት ተናግረዋል።
መንግስት ቅድሚያ ለሰላም ትኩረት በመስጠት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን መግለጻቸውን አስታውሰው፣ ህብረተሰቡም ሰላምን ለማጽናት ከመንግስት ጎን በመሆን የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል።