የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚያንጽ ወሳኝ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚያንጽ ወሳኝ መድረክ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበርና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚያንጽ ወሳኝ መድረክ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በተሰጡት ተጨማሪ የስምንት ወራት የስራ ጊዜ ቀሪ የምክክር ምዕራፎችን እንዲቋጭ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም መክረዋል።
ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባት መፍጠሪያ መሳሪያ መሆኑንና በበርካታ ሀገራት ተተግብሮ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ዳግማዊ ተስፋዬ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክር የአንድ ሀገር ዜጎች በመሰረታዊ የልዩነት ሃሳቦች ላይ መግባባት መፍጠሪያ መሳሪያ ነው።
ሀገራዊ ምክክር ዜጎች የሚያነሷቸውን ሃሳቦች በሰላማዊ መንገድ በምክክር የመፍታት ባህልን የሚያዳብር ከመሆኑ ባለፈ በሀገራቸው ጉዳይ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዜጎች መካከል መተማመንን ለማዳበርና ዲሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲያብቡ የሚያደርግ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የሃሳብ ድግስ ደግሳ ያላችሁን ሃሳብ ግለፁ ማለቷ አዲስ አካሄድ ነው ያሉት የታሪክ ተመራማሪው ይህ አካሄድ በተለያዩ ሀገራት ከዚህ ቀደም መተግበሩንም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የተሳታፊ ልየታና አጀንዳ ማሰባሰብ የተሳተፉት የውሃ ምህንድስና ተመራማሪው ሲሳይ ደመቁ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክር ሀገራት ችግሮችን በብዙሃን የህዝብ ድምፅ አቅጣጫ የሚያሲዙበት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብዝሃ ሃብትና ብዝሃ ማንነት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ሀገራዊ ምክክር ለቀጣይ ትውልድም ጭምር የሚጠቅም ችግራችንን አሸንፈን እንደዓድዋ በዓለም አደባባይ የምንታይበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ባሉት ጊዜያት አበረታች ስራዎችን ማከናወኑን አንስተው፤ በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ ቀሪ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።