ቀጥታ፡

የቡና ጥራትን በማሻሻል በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦የቡና ጥራትን በማሻሻልና አቅራቢዎች ምርቱን በቀጥታ ወደዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ በማስቻል በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገለጹ።  

የቡና አምራቾችና አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን የቡና ምርት በፍጥነት ወደ ገበያ ሊያቀርቡ ይገባል 

ባለፉት ሁለት ወራት የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ በመምጣቱ የቡና አምራቾችና አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን የቡና ምርት በፍጥነት ወደ ገበያ ሊያቀርቡ እንደሚገባም አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የዓለም አቀፉ የቡና ገበያ ሁኔታ እና የኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። 

በዚህ ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በመጠንና ጥራት የተሻለ ቡናን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢን ማግኘት ተችሏል። 

የቡና እሴት ሰንሰለትን ማሳጠር፣ የግብይት ስርዓቱን ማስተካከልና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ መዋቅራዊ ለውጦች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በዓመት ከ600 ሺህ ሜትሪክ ቶን ያልበለጠ ቡና ሲመረት መቆየቱን አስታውሰው፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ቡና መመረቱን ተናግረዋል።  

በ2017 በጀት ዓመት 470 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀው፣ በዘንድሮ በጀት ዓመትም 600 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

ከ2 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ቡናን ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የላኪ ፍቃድ ማግኘታቸውን ገልፀው፤ 500 ያህሉ ቀጥታ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል። 

ባለፉት ሁለት ወራት የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እየቀነሰ መምጣቱን አንስተው፤ የጥራት ደረጃን በማሻሻል፣ ስፔሻሊቲ ቡናን በማቅረብና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የታቀደውን ለማሳካት እንደሚሰራ ነው የገለፁት። 

ቡና በተመረተበት ዓመት መውጣት እንዳለበት በህግ የተቀመጠ ቢሆንም ምርት ዋጋ ይጨምራል በሚል ሃሳብ ይዘው የተቀመጡ በእጃቸው ላይ ያለውን መሸጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

ለአንድ ዓመት ያህል የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በዚሁ ሊቀጥል እንደሚችል ተገንዝበው በእጃቸው ያለውን ቡና በአፋጣኝ ለገበያ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል።  

ሀገራዊ የኮንትሮባንድ ግብረኃይል መቋቋሙን ጠቁመው፤ በኮንትሮባንድ ለመላክ ጥረት የሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርግም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም