ቀጥታ፡

የቡና አምራቾችና አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን የቡና ምርት በፍጥነት ወደ ገበያ ሊያቀርቡ ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የቡና አምራቾችና አቅራቢዎች በእጃቸው ያለውን የቡና ምርት በፍጥነት ወደ ገበያ ሊያቀርቡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አሳሰበ።

ባለፉት ሁለት ወራት የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱንም ዋና ዳይሬክተሩ አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) የዓለም አቀፉ የቡና ገበያ ሁኔታ እና የኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህ ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) እንዳሉት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በመጠንና በጥራት የተሻለ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት ተችሏል።

የቡና እሴት ሰንሰለትን ማሳጠርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ቡና መመረቱን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ከቡና ወጪ ንግድ ገቢ መገኘቱን ገልፀው፣ በዘንድሮ በጀት ዓመትም 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እየቀነሰ መምጣቱን አንስተው፤ የጥራት ደረጃን በማሻሻል፣ ስፔሻሊቲ ቡናን በማቅረብና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የታቀደውን ለማሳካት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ከ2ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ቡናን ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የላኪነት ፈቃድ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ 500 ያህሉ ቀጥታ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡና በተመረተበት ዓመት መውጣት እንዳለበት በህግ የተቀመጠ ቢሆንም ዋጋ ይጨምራል በሚል ምርት ይዘው የተቀመጡ አካላት ለአንድ ዓመት ያህል የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በዚሁ ሊቀጥል እንደሚችል ተገንዝበው በእጃቸው ያለውን ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ሀገራዊ የኮንትሮባንድ ንግድን የሚከላከል ግብረ ኃይል መቋቋሙን ጠቁመው፤ በኮንትሮባንድ ለመላክ ጥረት የሚያደርጉ አካላት ላይ ክትትል እንደሚያደርግም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም