ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ለከተሜነት መስፋፋት በትኩረት እየሰራ ነው

አዳማ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ለከተሜነት መስፋፋት፣ ለተሻለ እና ምቹ ኑሮ እውን መሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ፍትሃዊ የመሰረተ-ልማት ስርጭትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል

መድረኩ ከስድስት ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ከንቲባዎችና የዘርፉ አመራሮች ያዘጋጀው የ"ስማርት ሲቲ" ትግበራ እና የ"ፕሌስ ሜኪንግ" (ሁሉን አቀፍ የህዝብ ቦታዎች ልማት) ስልጠናዊ አውደ ጥናት በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ጤናው እንደገለጹት፤ መድረኩ በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ ከተሞችን በአባልነት በመያዝ፣ ለከተሜነት መስፋፋት፣ ለተሻለና ምቹ ኑሮ እውን መሆን በትኩረት እየሰራ ነው።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ መድረኩ ከተሞች ጽዱ፣ ውብና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ ከተሞች ያላቸውን ሀብት በአግባቡ አውቀው የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰባቸውን እንዲያሳድጉ አጋዥ እየሆነ ነው።

ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የ"ስማርት ሲቲ" አሰራርን በመዘርጋት የአገልግሎት ጥራትና የዜጎችን ደህንነት እንዲያረጋግጡ እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ከተሞችን መልካም ተሞክሮ በመቀመር የአቅም ግንባታ ስራዎችን እንዲያከናውኑ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም "ፕሌስ ሜኪንግ" የተሰኘው ስልጠና ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የህዝብ መዝናኛና መናፈሻ ቦታዎችን ለማልማት የሚረዳ ሲሆን፤ ይህም ባለፉት አራት ዓመታት በከተሞች ልማት የታየውን ተጨባጭ ለውጥ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።


 

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የጨለለቅቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ተስፋነህ ታደለ ፤ አስተዳደሩ ጨለለቅቱ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል። 

ይህ ስልጠና እንቅስቃሴያችንን በቴክኖሎጂ ለማሳለጥ ተጨማሪ አቅም ይሆነናል ሲሉም ተናግረዋል።

የቦዲቲ ከተማ ከንቲባ አቶ ዘካርያስ ጃታ በበኩላቸው፤ መድረኩ እንደ ሀገር የተጀመሩ የከተማ ኮሪደር ልማት ኢንሼቲቮችን ለመደገፍና ከተሞችን በዲጂታላይዜሽን መርህ ወደ ስማርት ሲቲ ለመቀየር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ተሳታፊ ከንቲባዎች ከስልጠናው የሚያገኙትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም፣ በከተሞቻቸው የሚታየውን የገቢ አሰባሰብና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም