ቀጥታ፡

ፍትሃዊ የመሰረተ-ልማት ስርጭትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት ፍትሃዊ የመሰረተ-ልማት ስርጭትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት ማከናወኑን የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ  ሳኒ ገለፁ። 

የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ አጋሮችና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር በመተባበር የሚያካሂደውን የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። 

የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ "ኢትዮጵያ ትገነባለች ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ጥራት ለመሰረተ ልማት እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ ከሚያዝያ 9 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት በአዲስ ዓለም አቀፍ  ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ተገልጿል። 

በዚህ ወቅት የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት የመሰረተ-ልማትና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። 

ዘርፉ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል የሚያሳትፍና ሰፊ የስራ እድሎችን በመፍጠር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማደግ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልፀዋል። 

መንግስት ፍትሃዊ የመሰረተ-ልማት ስርጭትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የኃይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦች እንዲሁም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሀገሪቱ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት ሀገሪቱ በመሰረተ-ልማት ዝርጋታ ያሳካችውን ስኬቶችና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎችና ቀጣይ ትልሞች የሚቀርብበት መድረክ እንደሚሆን ተናግረዋል። 

ለአራት ቀናት በሚካሄደው መርሃግብር የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተዋናዮች፣ የፈጠራ ባለቤቶችና የግንባታ ግብዓት አቅራቢዎች ይሳተፋሉ ብለዋል። 

መርሃግብሩ የግንባታ እቃዎችና ማሽነሪዎች እንዲሁም ዲጂታል የግንባታ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት መሆኑን ጠቁመዋል። 

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት እስከ 20 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልፀው፤ በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት እድገትና የብልፅግና ጉዞ መሰረት ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። 

ሀገሪቱ ባላት የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ተኪ ምርት ምርታማነትን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

የተሻለ አፈፃፀምና አደረጃጀት ያላቸው ተቋራጮችና አማካሪዎች እውቅና የሚሰጥበትና በኮንስትራክሽን ዘርፉ አዳዲስ አሰራሮችና የግንባታ ዘዴዎች እንዲተዋወቁ የሚያደርግ እንደሚሆንም ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም