ቀጥታ፡

የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም የምርጫ ቦርድን የምርጫ አስተዳደር አቅም በመገንባት ጤናማ የፖለቲካ ፉክክር እንዲፈጠር እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የምርጫ አስተዳደር አቅም በማጎልበት ጤናማ የፖለቲካ ፉክክር እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ ገለጹ። 

በሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ ላይ ከምርጫና ወንጀል ሕጉ በተፃራሪነት ሊፈጸሙ የሚችሉ የሕግ ጥሰቶች ላይ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን እየሰራ እንደሚገኝ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

በዚህም በቦርዱ ዕውቅና አግኝተው የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ለመፎካከር የምርጫ ምልክትና ርዕዮተ ዓለማቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ምርጫ ቦርድ ስኬታማ የሪፎርም እርምጃ ከተከናወነባቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

በምርጫ ቦርድ የተከናወነው መሠረታዊ የለውጥ እርምጃ በገለልተኝነት ምርጫን ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ምቹ ምኅዳር በመፍጠር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ቁልፍ ሚና እንዲወጣ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎችና የኃላፊዎች የሹመት ገለልተኝነትም በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ጤናማ የፉክክር ምኅዳር በመፍጠር ወሳኝ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል። 

ይህም በኢትዮጵያ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ጤናማ የፖለቲካ ፉክክርና የምርጫ አስተዳደር አቅም በመፍጠር በመርህ ላይ የተመሰረተ ተቋምና ሥርዓት መገንባት ማስቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።

በዚህም በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተገኙ ልምድና ተሞክሮዎችን በመቀመር ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚከናወነው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመድገም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት በኩልም የምርጫ ሂደቱን ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛነት ለማረጋገጥ ለምርጫ ቦርድ፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተገቢው ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነት በሂደቱ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫም በኢትዮጵያ የተሻለ የዴሞክራሲ ባህል መገንባት የሚያስችል ምኅዳር ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በምርጫው ለህዝብና ሀገር የሚጠቅም ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት መንፈስ መሳተፍ ከቻለ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛነት አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ከምርጫና ከወንጀል ሕጉ በተፃራሪነት ሊፈጸሙ የሚችሉ ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ ተቋማት ምክክር በማድረግ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም