የኃይማኖት አባቶች በልማትና ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን የላቀ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት አባቶች በልማትና ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን የላቀ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
ባህርዳር፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት አባቶች ትውልድን ከማነጽ ባለፈ በልማትና ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን የላቀ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ''በመደመር መንግሥት እይታ የኃይማኖት መሪዎች ሚና'' በሚል መሪ ሀሳብ በባህር ዳር ከተማ ከእስልምና ኃይማኖት አባቶች ጋር በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ያለውን ብዝሃ ኃይማኖት፣ ቋንቋና ማንነት ለላቀ ሀገር ግንባታና ጥንካሬ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በተለይም የኃይማኖት ተቋማት ታሪክንና ቅርስን ጠብቆ ለትውልድ በማሸጋገር ረገድ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁሉም የኃይማኖት አባቶች ትውልድን ከማነጽ ባለፈ በልማትና የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን የላቀ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።
በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማትና የሰላም ግንባታ ሂደቶች ለስኬት እንዲበቁ ህዝቡ በጋራ መቆም እንዳለበት አንስተው ለዚህም የኃይማኖት አባቶች ትልቅ አደራ አለባችሁ ብለዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ እሸቱ የሱፍ(ዶ/ር)፤ የኃይማኖቶች ተቀዳሚ ዓላማ ሰላም፣ አብሮነት፣ ፍቅርና አንድነትን ማጽናት በመሆኑ በዚሁ መሰረት አባቶች ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ መንግስት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።