በኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 65 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 65 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 65 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ እድሪስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ለዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚደረገው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 46 በመቶ እንደነበር አስታውሰው በንቅናቄውና በመንግስት የተቀናጀ ድጋፍ አቅሙን ወደ 65 ነጥብ 4 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
መንግስት ለዘርፉ አስፈላጊውን ሁሉ ማዘጋጀቱ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ግንባታቸውን አጠናቀውና ማሽነሪዎችን አስገብተው ወደ ስራ እንዲገቡ ማስቻሉ ለስኬቱ መሠረት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
ከመሰረተ ልማትና የሰው ኃይል አኳያ አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መከናወኑን ጠቅሰው ክህሎት ያለው የሰው ኃይል በማቅረብ ረገድም ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለዘርፉ ሰፊ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲመቻች እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ተግዳሮቶችን በቅርበት የመከታተልና የመፍታት ባህል መዳበር በመንግስትና ባለሀብቶች መካካል ያለው መቀራረብ ይበልጥ እንዲጎለብት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በክልሉ 300 የሚሆኑ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማሽነሪዎቻቸውን በማስገባት ወደ ስራ መግባታቸው ከታዩ ስኬቶች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ክልሉ አዳዲስ አምራቾችን ለመቀበል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው በገዳ ስፔሻል የኢኮኖሚ ዞን 25 ሺህ ሄክታር የተሟላ መሰረተ ልማት ያለው መሬት ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በቡልቡላ እና ነቀምቴ የተቀናጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለባለሀብቶች የሚሆኑ መሬት መዘጋጀታቸውን ጠቁመው በአዳማ፣ ሸገር፣ ቢሾፍቱ እና ሞጆ ከተሞችም አስፈላጊው ሁሉ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
ክልሉ የአሰራር ቢሮክራሲን በማሳጠርና የባለሀብቶችን ቅሬታ ወደ ዜሮ በማውረድ አዳዲስ ባለሀብቶችን ለመቀበል ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አረጋግጠዋል።