ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚደረገው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚደረገው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገለፁ።
በኢትዮጵያ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው
የብሄራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሸገር፣ በቢሾፍቱ እና በአዳማ ከተሞች በሚገኙ ልዩ ልዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
የመስክ ምልከታው በኢንዱስትሪዎች አካባቢ ያሉ ማነቆዎችን በቅርበት ለመረዳትና በካውንስሉ አማካኝነት ፈጣን መፍትሄ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የካውንስሉ አባል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባንኩ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።
ባንኩ በዘርፉ ያሉ እውነተኛ ችግሮችን በመለየት በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ በኩል የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚሰጠው አጠቃላይ ብድር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የኢንዱስትሪ ፋይናንስ እንደሆነ ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።
ከባንኩ የብድር ሴግሜንቶች መካከል ከ45 በመቶ በላይ የሚሆነው ለአምራች ኢንዱስትሪው የቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል።
አምራች ድርጅቶች አሁንም ተጨማሪ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚፈልጉ የገለጹት አቶ አቤ ሳኖ፣ ባንኩ ይህንን ፍላጎት ለመሙላት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።
አጠቃላይ የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ ይፈልጋል፤ እኛም የተሻለ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ተረድተናል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።