ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን ባህላዊ እሴቶቻቸውን በአደባባይ በመግለጥ የህዝብና የሀገር ሃብት እንዲሆኑ መደላድል ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ለባህል ልማት በተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያውያን ባህላዊ እሴቶቻቸውን በአደባባይ በመግለጥ የህዝብና የሀገር ሃብት እንዲሆኑ መደላድል መፈጠሩን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሃብቶችን በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት።

በንባብ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-መጻሕፍት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል

ለአብነትም የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስታት፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የአክሱም ሃውልት፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የኮንሶ ባሕላዊ መልክዓ ምድር፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድር በሚዳሰሱ የዓለም ቅርስነት አስመዝገባለች።

በማይዳሰሱ ቅርስነትም የመስቀል በዓል አከባበር፣ የፊቼ ጫምባላላ በዓል፣ የገዳ ሥርዓት፣ የጥምቀት በዓል አከባበር፣ የሹዋል ኢድ እና የወላይታ ጊፋታ በዓላት የማህበረሰቡን ዕሴቶች፣ በዓላት፣ ወጎችና ጥበቦች በመግለጥ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤም በቱሪዝም፣ በትውልድና በሀገር ገጽታ ግንባታ አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል። 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የእምቅ ሕብረ ብሔራዊ ባህልና ዕሴት መገኛ ምድር ናት።

በሕብር ያሸበረቁ የዜጎች ብዝኅ ኃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችም የህዝብ ለህዝብ አብሮነትና ትስስርን በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በአደባባይ የሚያከብሯቸው የህዝብ በዓላትም አብሮነትና አንድነትን ከማጎልበት ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የዜጎች ባህላዊ ዕሴቶች ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የበለጠ ለማጎልበት ቀጣይነት ያለው የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የለውጡ መንግስት ለባህል ልማት የሰጠው ትኩረትም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ እሴታቸውን በአደባባይ በመግለጥ የህዝብና የሀገር ሃብት እንዲሆኑ ማስቻሉን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የባህል ማዕከላትን በመገንባት የዜጎችን ባህላዊ ዕሴት በሚገልጡ ቅርሶችና ቅርፃ ቅርፆች በማስዋብ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተገነቡ ሀገር አቀፍ የልማት ፕሮጀክቶችም የህዝብን ባህላዊ ዕሴትና የአኗኗር ዘይቤ የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህላዊ ዕሴቶች በአደባባይ በመግለጥና አሰባሳቢ ትርክትን በማጎልበት ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

በአደባባይ የሚከበሩ ባህላዊ ዕሴቶችም የኢትዮጵያዊያንን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በማጉላት ሀገራዊና የዓለም አቀፍ የትውውቅ መድረክ እየፈጠሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ጨምሮ የመስቀል፣ የጥምቀት፣ የኢሬቻ፣ የፊቼ ጫምባላላ፣ የሹዋል ኢድና የወላይታ ጊፋታ የአደባባይ በዓላት የዜጎች የአብሮነት መድረክ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም