በንባብ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-መጻሕፍት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በንባብ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-መጻሕፍት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል
አርባ ምንጭ ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በንባብ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር መንግስት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-መጻሕፍት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
"የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የንባብ ሳምንት ፣ኤግዚቢሽን ፣ስልጠናና ፓናል ውይይት መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ፈተናዋን የተሻገረች ተስፈኛ ሴት ማፍሪያ ማዕከል የሆነው - ለነገዋ
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግስት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-መጻሕፍትን ተደራሽነት ለማስፋት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በንባብ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር መንግስት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-መጻሕፍት ማስፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንና ለዚህም በአዲስ አበባ የሚገኘው አብርሆት እና በድሬዳዋ የሚገኘው እመርታ ቤተ-መጻሕፍትን ለአብነት አንስተዋል።
የንባብ ባህል መዳከም በትምህርት ጥራት ላይ የራሱን አሉታዊ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ጠንካራ የንባብ ባህልን በማዳበር ረገድ ወላጆችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አባተ ካሣው በበኩላቸው፣ ተቋሙ ላለፉት 83 ዓመታት ትውልድን የማንቃት ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በንባብ ሳምንት መርሃ-ግብር ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከ4 ሺህ በላይ መጻሕፍት በክልሉ ለሚገኙ ቤተ-መጻሕፍት፣ ትምህርት ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች ይበረከታሉ ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ ኦይቻ መድረኩ የሚያነብ ትውልድ በመፍጠርና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጉልህ አበርክቶ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ተወካይ ሊዲያ ከንቲባ በበኩላቸው መርሃ-ግብሩ የሚያነብና ታሪክን የሚሰንድ ትውልድ በመፍጠር ረገድ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
አንባቢ ትውልድ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ መሰረትን የሚጥል መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ፣ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው መርሃ-ግብርም ለሚቀጥሉት 5 ቀናት ይቆያል።