ቀጥታ፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር መሠረት ያደረጉ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

አዳማ ፤ የካቲት 25/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር መሠረት ያደረጉና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የማፍላት ስራ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በምስራቅ ቦረና ዞን የእንስሳት መኖ እጥረት እንዳያጋጥም የመኖ ልማት ስራ ከተፋሰስ ጥበቃ ጋር ተቀናጅቶ እየተከናወነ ነው

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ሃገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሐምሌ 2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና የጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዞኑ 11 ወረዳዎች ባሉ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ለመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ ተጀምሯል።


 

ችግኝ ጣቢያዎቹ ለአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን አፍልቶ በማቅረብ ረገድ እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል።

ዘንድሮም ለማዘጋጀት ከታቀደው ከ284 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ውስጥም 241 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኞችን የማፍላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቀሪ ችግኞችን የማፍላት ሥራም እስከ መጪው ግንቦት ወር ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በችግኝ ዝግጅቱም በአብዛኛው የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ለሚያገለግሉ የደን እና ጥምር ደን ዝርያዎች ትኩረት የተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚያስገኙና እና ለምግብነት የሚውሉ 26 ነጥብ 7 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኞችን ያካተተ የዘር ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

የዘንድሮ ዓመት የችግኝ ተከላ የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር መሠረት በማድረግ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመው በዞኑ ባለፉት ዓመታት ከተተከሉ ችግኞች ከ85 በመቶ  በላይ መጽደቃቸውን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም የተተከሉ ችግኞችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው ያረጋገጡት።

በዘንድሮው ዓመት በዘርፉ የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካትም የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ተቆፍረው መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም