በምስራቅ ቦረና ዞን የእንስሳት መኖ እጥረት እንዳያጋጥም የመኖ ልማት ስራ ከተፋሰስ ጥበቃ ጋር ተቀናጅቶ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን የእንስሳት መኖ እጥረት እንዳያጋጥም የመኖ ልማት ስራ ከተፋሰስ ጥበቃ ጋር ተቀናጅቶ እየተከናወነ ነው
ነጌሌቦረና፤የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ቦረና ዞን የእንስሳት መኖ እጥረት እንዳያጋጥም የመኖ ልማት ስራ ከተፋሰስ ጥበቃ ጋር ተቀናጅቶ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ኩልሌ ሸና እንደገለጹት፤ ዞኑ ቆላማና ዝናብ አጠር በመሆኑ በየጊዜው የሚያጋጥመውን የእንስሳት መኖ እጥረት በዘላቂነት ለመቋቋም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በዘንድሮው የበጋ ወቅት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ 105 ተፋሰሶችን መሠረት ያደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ ተፋሰሶች ላይ የሚካሄደው የተቀናጀ የልማት ሥራ ከ52 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት የሚያካልል መሆኑን አቶ ኩልሌ ጠቁመዋል።
ከዚህ ውስጥ በሰው ሰራሽ ጫና እና ከልክ ያለፈ ግጦሽ የተራቆተ ከ38 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተከልሎ መልሶ እንዲያገግም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተከናወነው እንቅስቃሴ 24 ሺህ 430 ሄክታር የግጦሽ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተከልሎ እንዲያገግም የተደረገ ሲሆን፣ ይህም መኖን በዘላቂነት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።
ከተፈጥሮ ግጦሽ በተጨማሪም በክረምትና በበጋ መስኖ የታገዘ የመኖ ልማት ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል።
በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የአፈርና የድንጋይ እርከን እንዲሁም የጎርፍ መፋሰሻ ቦይ ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ዝግጅትንም ጠቅሰዋል።
በነዚህ የልማት ሥራዎች ላይ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች በንቃት ተሳትፈዋል።
ከዚህም ባለፈ በበልግና በክረምት የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ወርቁ አለባቸው በሰጡት አስተያየት፤ አካባቢያቸው ዝናብ አጠር በመሆኑ በተደጋጋሚ ለሚከሰተው የእንስሳት መኖ እጥረት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ከደረሰባቸው ጉዳት በመማር አሁን ላይ በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ አቶ አልዬ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ እና የእንስሳት መኖ ልማት ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርቅንና የአካባቢ መራቆትን ለመቋቋም በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።