የፍትሕ ሥርዓት ሪፎርም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ገንቢ ሚና እንዲወጡ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፍትሕ ሥርዓት ሪፎርም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ገንቢ ሚና እንዲወጡ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦የፍትሕ ሥርዓቱ ሪፎርም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ገንቢ ሚና የሚወጡበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ ገለጹ።
አምስተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት "ራስን መቻል፤ ለዘላቂ ሰላምና ለአካታች ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ከየካቲት 26 እስከ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል።
በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ
የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የተወሰዱ የሕግና የአሰራር ማሻሻያዎች በሲቪክ ምኅዳሩ ላይ አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል።
በዚህም ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም፣ በልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚኖራቸውን ሚና በማሳደግ በነፃነት ተደራጅተው የሚሰሩበት ምኅዳር መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ዓ.ም የመደራጀት ነፃነትና መብትን የሚያጎናጽፍ ምኅዳር መፍጠር ያስቻለ የአሰራር ሥርዓት እንደሆነም ተናግረዋል።
በኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተካሄደው የሪፎርም እርምጃም ለመደራጀት መብት ምቹ መደላድልን በመፍጠር መሠረታዊ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ይታዩበት የነበረውን ቁጥጥርን ማዕከል ያደረገ ዕይታ በመቀየር መደራጀት ለሚሹ ዜጎች አስቻይ የስራ ምኅዳር መፍጠሩን አንስተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በሕገ-መንግስቱ የተቀመጠውን የመደራጀት መብትና ነፃነት የሚቃረኑ አሰራሮች እንደነበሩ ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ አዋጁ መተግበሩም የማህበረሰብ ድርጅቶችን የአሰራር ዕይታ ቀይሯል ብለዋል።
በፌዴራል ደረጃ የተደረገው የሕግና የአሰራር ማሻሻያም በክልሎች ጭምር ክትትል በማድረግ በርካታ አዳዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወደስራ የገቡበትን ዕድል እንደፈጠረም አንስተዋል።
በዚህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም በተለያዩ የልማት መስኮች የሥራ አድማሳቸውን የሚያሰፉበት አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
ለአብነትም በ2013 ዓ.ም ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተጫወቱት ገንቢ ሚና ተጠቃሽ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ መሆኑን አስታውሰዋል።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬትም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚሰሩ ድርጅቶች ካለፈው ምርጫ ካገኙት ተሞክሮ በመነሳት ገንቢ ሚና ይወጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ይህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የነበረባቸውን አሳሪ የሕግና የአሰራር ሥርዓት ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማነት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
በየዓመቱ የሚካሄደው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንትም የመንግስትና ባለድርሻ አካላትን ትብብርና አጋርነት በማጠናከር የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ የሚደረግበት ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘንድሮም ከየካቲት 26 እስከ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ አምስተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት "ራስን መቻል፤ ለዘላቂ ሰላምና ለአካታች ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚካሄደው መድረክም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የመንግስት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንቱም የመንግስትና ባለድርሻ አካላትን ትብብር፣ ቅንጅትና ትስስር በማጠናከር የተሻለ የልምድ ልውውጥ፣ የፖሊሲና የተግባር ግብዓቶችን ለማቅረብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።