ቀጥታ፡

በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ  

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦ በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።  

መድረኩ "የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ!" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል   

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት፣ ሚኒስትሮች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት አመራሮች፣ የፍትህ አካላት፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።  


 

መድረኩ በዋናነት በሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት እና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ተቋማት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት በቀጣይ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ በሚያረጋግጡባቸው ጉዳዮች ላይ በዝርዝር እንደሚመክር ተገልጿል።  

እንዲሁም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል።   

እነዚህ ተቋማት ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበሩባቸውን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች፣ ከለውጡ ወዲህ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶችና ያጋጠሟቸውን እንቅፋቶች በመለየት የቀጣይ የጋራ የሥራ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።  


 

የፍትህ አካላት ገለልተኝነትና የዴሞክራሲ ተቋማት ጥንካሬ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር ወሳኝ መሆናቸው ተመላክቷል።    

የተቋማቱን የሥራ ቅንጅት ማጠናከር ለሀገራዊ ሪፎርሙ ስኬታማነትና ለተቀናጀ የሀገር ግንባታ ሂደት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።  

ተቋማቱ ያላቸውን ጥንካሬና ድክመት በመገምገም በገለልተኝነትና በብቃት ሕዝባዊ አደራቸውን እንዲወጡ የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ መፍጠር የመድረኩ ዋነኛ ግብ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም