ቀጥታ፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ 30 ሚሊዮን የገጠር መሬት ማሳዎች በዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ተመዝግበዋል

ቦንጋ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ 30 ሚሊዮን የገጠር መሬት ማሳዎች በዲጂታል የመረጃ ሥርዓት መመዝገባቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና አገልግሎቶችን ከዲጂታል መታወቂያ ጋር የማስተሳሰር ተግባር እየተከናወነ ነው

የግብርና ሚኒስቴር ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመተባበር  ''ዲጂታል ማንነት ለተረጋገጠ ይዞታ ባለቤትነትና ለላቀ የፋይናንስ ተጠቃሚነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ትዕግስቱ ገብረ-መሥቀል እንደገለጹት፣ ሀገራዊ የገጠር መሬት አስተዳደር ሥርዓቱን ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ 50 ሚሊዮን ማሳዎች ውስጥ እስካሁን ድረስ 30 ሚሊዮን የሚሆኑት በዲጂታል መረጃ ሥርዓት ተመዝግበው አርሶ አደሩ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል።

የመረጃ ማዘመን ስራው በአሁኑ ወቅት በ516 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉንም ነው ያመለከቱት።

አርሶ አደሩ መሬቱን በዋስትና በማስያዝ እስካሁን 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የብድር አገልግሎት ማግኘት መቻሉንም አብራርተዋል።

በተያዝነው በጀት ዓመት 12 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፣ የመረጃ ስርዓቱን ከዲጂታል መታወቂያ ጋር ማስተሳሰር አካታች የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የዲጂታል መታወቂያ ከይዞታ ማረጋገጫ ጋር መገናኘቱ አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በክልሉ የታቀደውን ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሀብታሙ ካፍትን እና የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፣ የዲጂታል አሰራሩ ለዓመታት ሲነሳ የነበረውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንደሚቀርፍ ጠቁመዋል። 


 

መረጃን በዘመናዊ መልኩ ማደራጀትና አርሶ አደሩን የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ማድረግ ላይ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።


 

በመድረኩም የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ሃላፊዎች፣ የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮ ፖስታ አገልግሎት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም