የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ሕፃናት የሕክምና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ሕፃናት የሕክምና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ሕፃናት የሕክምና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስታወቁ።
በአማራ ክልል የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው
"የላቀ ተደራሽነትን ለኢትዮጵያ ልጆች፤ በመከላከል፣ በሕክምና እና በማካተት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሀሳብ፣ ሀገር አቀፍ የአፈጣጠር ችግር የሕክምና አገልግሎት ሳምንት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአፈጣጠር ችግርን ለመከላከል ሕፃናት ከመፈጠራቸው በፊት እና በእርግዝና ወቅት የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ወሳኝ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እናቶች ከመፀነሳቸው በፊት እና በእርግዝና ወቅት የፎሊክ አሲድ ንጥረ ነገርን እንዲወስዱ ማስተማር እንዲሁም አመጋገብ ችግርን ቀድሞ ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስት ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሕፃናት እንደተወለዱ ችግሮቻቸውን በፍጥነት በመለየት አስፈላጊውን የቀዶ ሕክምና እና ሌሎች ወቅታዊ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
አገልግሎቱን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ለማጠናከርና የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ደረጀ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ሕፃናት እንደ ማንኛውም እኩያዎቻቸው ትምህርት ቤት እንዲገቡና እኩል ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የመላው ማኅበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በጤና ሚኒስቴር የስፔሻሊቲ እና ተሀድሶ አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ ኤርሚያስ ሙላቱ በበኩላቸው፤ በችግሩ ዙሪያ ሰፊ የማኅበረሰብ ግንዛቤ የመፍጠርና ህክምና የመስጠት ስራ ባለፉት አመታት በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ሀገር አቀፍ የአፈጣጠር ችግር የሕክምና አገልግሎት ሳምንት ተከትሎ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የግንዛቤ እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
ይህ በየዓመቱ የሚከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት፣ በአፈጣጠር ችግር ዙሪያ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየርና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገልጿል።