በአማራ ክልል የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው
ባህርዳር፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በሀገሪቱ የተዘረጋው ጠንካራ የጤና ሥርአት ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት አስችሏል
በክልሉ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከል አቅም ማጎልበት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በክልሉ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ስጋቶችን በጥናት በመለየት የቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
እንደ ወባ፣ ኮሌራና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመቀነስ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ሕብረተሰቡ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስድ ከማድረግ ባለፈ፣ ከአቅም በላይ የሆኑ የጤና ችግሮች ሲከሰቱ ፈጣን የሕክምና ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ለቀጣዮቹ የበልግና የክረምት ወራት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ እንደ ኮሌራ፣ ወባ እና ኩፍኝ የመሳሰሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ የሕክምና ግብዓቶችና የሰው ኃይል ዝግጅት መጠናቀቁንም ነው ያብራሩት።
የሰሜን ሸዋና ሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ተወካዮች በበኩላቸው፣ በየዞኖቻቸው የሚታዩትን የወባ እና የኮሌራ በሽታ ስጋቶች ለመቀነስ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መቆጣጠር ኬዝ ቲም አስተባባሪ በላይሁን ከበደ፤ በዞኑ በበልግና ክረምት ወራት ሊፈጠር የሚችለውን የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ስጋት አስቀድሞ ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ የሕብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኬዝ ቲም አስተባባሪ አባይነህ ታረቀኝ፤ በዞኑ ለኮሌራም ሆነ ለወባ በሽታ የመጋለጥ ስጋቱ ከፍተኛ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።