በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ስርጭትና መጠን ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ስርጭትና መጠን ይጠናከራል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦በቀጣዮቹ አስር ቀናት በሀገሪቱ የበልግ ሰብል አብቃይ አካባቢዎች የዝናብ መጠንና ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋና እየተጠናከረ እንደሚሄድ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ አራተኛውን የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ሊያስጀምር ነው
በኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ፣ምክር አገልግሎት እና ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለዝናብ መፈጠር ምቹ የሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እየተጠናከሩ መሆናቸውን የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የዝናብ ስርጭቱ የሚሸፍናቸው ደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ (ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች)፣ የስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች፣ የመካከለኛውና የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ምስራቅና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በአብዛኛው ስፍራዎች የዝናብ መጠኑ መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንደሚሆን ገልጸው፤አልፎ አልፎም ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።
የዝናቡ መሻሻል በተለይም ለበልግ አብቃይ አርሶ አደሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
በበልግ እየጣለ ያለው ዝናብ የማሳ ዝግጅትና ዘር፡ የአፈር እርጥበትን በማሻሻል አርሶ አደሩ የተለያዩ ሰብሎችን መዝራት እንዲችል ምቹ ሁኔታን በመፍጠር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ለቋሚ ተክሎች፡ ቀደም ብለው ለተዘሩ የበልግ ሰብሎችና በአካባቢው ለሚገኙ ቋሚ ተክሎች ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦም ገልጸዋል።
ለውሃ አጠር አካባቢዎችም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚጥለውን የዝናብ ውሃ በማሰባሰብና በማከማቸት ለቀጣይ እንዲጠቀም ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
በበልግ የሚጥለው ዝናብ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የገጸ ምድር ውሃ መጠን በተለያዩ ተፋሰሶች ላይ እንደሚጨምርም ገልጸዋል።
በዚህም ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛውና መካከለኛው አዋሽ፣መካከለኛና ታችኛው አባይ፣ ገናሌ ዳዋ እና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች የተሻለ እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብለዋል።
በዚህም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን በመጠቀም የውሃ መጠናቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ከፍተኛ የቀን ሙቀት እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በዚህም በጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ምዕራብ አማራ አካባቢዎች የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ33 እስከ 37 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊደርስ እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ተብሏል።