ኢንስቲትዩቱ አራተኛውን የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ሊያስጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ አራተኛውን የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ሊያስጀምር ነው
ዳንቦያ፤ የካቲት 24/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከንባታ ዞን አራተኛውን ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር የመትከል ተግባርን በማጠናቀቅ ስራ ለማስጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ከንባታ ዞን ዳንቦያ ወረዳ ዳቶ ዳርሀቦራ ተራራ ላይ ነው ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳሩን የተከለው።
ራዳሩ በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ያለን የአየር ሁኔታ መረጃ የመሰብሰብ አቅም ያለው ሲሆን፣ የትንተናና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን በተሻለ ጥራት ለመከወን ያስችላል ብለዋል።
በ14 ሜትር ከፍታ ላይ የተተከለው ይህ ራዳር የዝናብ መጠንን፣ የንፋስ ፍጥነትን፣ የዳመና እንቅስቃሴንና ዝናብ ያዘለ አውሎ ነፋስን የመሳሰሉ መረጃዎችን ከርቀት በመቃኘት ለዋናው የዳታ ማዕከል መረጃ ያስተላልፋል ብለዋል።
ይህ የራዳር ጣቢያ በኢትዮጵያና በፊንላንድ መንግሥታት ድጋፍ 13 ሚሊዮን ዩሮ በሚጠጋ በጀት ወደ ሥራ ከሚገቡ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመንና የተሳለጠ መረጃ ለማቅረብ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አብራርተዋል።
በፕሮጀክቱ የተጠቀሰውን ጨምሮ አራት የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳሮች፣ 10 የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያዎች፣ 10 የመብረቅ መከታተያና ሌሎች የተቀናጁ የሚቲዎሮሎጂ መሠረተ ልማትን የመገንባት ሥራን ያካተተ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ12 ስልታዊ ቦታዎች ላይ የራዳር ጣቢያዎችን ለመትከል እቅድ መያዙን ጠቁመው፤ አራተኛውን ጣቢያ በማጠናቀቅ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎቱን የማሳደግ አቅሙን አንደሚያጠናከር አስረድተዋል።
ራዳሩ በተተከለበት አካባቢ የኃይል መቆራረጥም ሆነ የመረጃ ልውውጥ እንዳይቋረጥ የፀሐይ ብርሃን ኃይል (ሶላር ኢነርጂ) እየተገጠመ ይገኛል ብለዋል።
የፕሮጀክቱን የመጨረሻ ምዕራፍ ለመጎብኘት በስፍራው የተገኙት በፊንላንድ ኤምባሲ የትብብር ዘርፍ ኃላፊ ቶሚ ሳርኪኦጃ መንግሥታቸው የኢትዮጵያን ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በመደገፉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።