የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።
ሰላም ሚኒስቴር ከሴቶች አደረጃጀት ጋር በመተባበር "በሴቶች ተሳትፎ የጸናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ ሀገራዊ የንቅናቄ መርሃ ግብር እያካሄደ ይገኛል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በተግባር የሚረጋገጠው የሴቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስራዎች ማዕከል ማድረግ ሲቻል ነው ብሎ ያምናል።
መንግሥት የሴቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ ስብራቶችን በመጠገን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና ውክልና አንዱ ስብራት መሆኑን በመገንዘብ የሴቶች አመራር ሰጪነት ለሀገር ግንባታ ፅናትና ለዘላቂ ብሄራዊ መግባባት የማይናወጥ መሰረት የሚጥል መሆኑን በመገንዘብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በፌዴራል ካቢኔ የሴቶች ስብጥር 50 በመቶ በማድረስ ዓለምአቀፍ እውቅና መገኘቱን አንስተው፤ የሴቶችን ቁልፍ አመራር ሰጪነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ፍሬያማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
የኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን ሴቶች የኢኮኖሚ ዋልታና የምርታማነት ሞተር እንዲሆን ማስቻል አስፈላጊ መሆኑን በማመን በተሰራው ስራ 6 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሴቶች የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ማግኘታቸውን አብራርተዋል።
በተለያዩ የልማት መርሃግብሮች ሴቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አንስተው፤ ይህም ሴቶች የሀገራዊ ምርታማነት መሰረት እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
በማህበራዊ ፍትህ የነበረውን ስብራት ለመጠገን በተሰራው ስራም እኩልነትና ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
በትምህርት፣ በጤና እና በማህበራዊ ጥበቃ በርካታ ሴቶችን የለውጡ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት አቶ አደም ፋራህ በመልዕክታቸው።
መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገርና ብልፅግና ፅኑ መሰረት የሚይዘው በሴቶች ግንባር ቀደም ሚና መሆኑን ያምናል ሲሉም ገልጸዋል።
መንግሥት ለዳበረ ዲሞክራሲ ግንባታና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ሰላም ለሰው ልጅ ህልውና መሰረት መሆኑንና ሰላማዊ ማህበረሰብ የሞራል ልዕልና መገለጫ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለንተናዊ ሰላም የሚረጋገጠው በሁሉም አካላት ርብርብ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሴቶች ለማህበረሰብ ሰላም ካላቸው ሚና ባለፈ የሰላም አርበኞችን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።