ኢትዮጵያ ከዘላቂ ልማትና ከአረንጓዴ የኢኮኖሚ እድገት ጋር የተጣጣሙ የአካባቢ ጥበቃ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዘላቂ ልማትና ከአረንጓዴ የኢኮኖሚ እድገት ጋር የተጣጣሙ የአካባቢ ጥበቃ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከዘላቂ ልማትና ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ እድገት ጋር የተጣጣሙ የአካባቢ ጥበቃ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።
የዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማትና በታዳሽ ኃይል ለዓለም የስኬት አርዓያ ሆናለች -የሮማኒያ አምባሳደር
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት፥ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሥነ-ሕይወት መጥፋት እና ብክለት በምድራችን የአካባቢ ደህንነት፣ የምግብ ዋስትና እና የልማት ጉዞ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ በምስራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ ድርቅና የአካባቢ መራቆት በማህበረሰቡና በስርዓተ ምህዳሩ ላይ አስከፊ ጉዳት እያስከተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አካባቢን መጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የህልውና ጉዳይና የብልጽግና መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ለአፍሪካና ለዓለም ምሳሌ የሚሆን አኩሪ የአረንጓዴ ልማት ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ከዘላቂ ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ከመገንባት ጋር የተጣጣሙ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎቿ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታላቅ የደን ልማት ለዓለም ማሳየቷንም አንስተዋል።
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የታዳሽ ሃይል ልማት ፕሮጀክቶች፣ የከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ እና ሌሎችም የልማት ኢኒሼቲቮች ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ዘላቂ ዕድገት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
የአውደ ጥናት የምክክር መድረኩ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዙሪያ የትብብር ሥራዎችን በማስፋት የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚበጁ ምክር ሀሳቦችን ለማመንጨት እንደሚረዳ አንስተዋል።
የዓለም አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የአፍሪካ አስተባባሪ ጆንኪ ቴኑ በበኩላቸው፤ ምስራቅ አፍሪካ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እና እምቅ አቅም እንዳለው ጠቅሰው፥ ይሁን እንጂ እንደ ብዝሃ-ህይወት መጥፋት፣ የመሬት መራቆት እና ብክለት ያሉ ፈተናዎች የተደቀኑበት ቀጣና ነው ብለዋል።
በመሆኑም ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመቋቋም በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።